አዲስ አበባ፣ ህዳር 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ኮምቦልቻ ወረዳ የገጠር መሬት የካዳስተር ሥራ የይዞታ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ለአርሶ አደሮች የመስጠት ስነስርዓት ተካሂዷል።
በዞኑ ፈዲስ፣ ቀርሳ፣ ኮምቦልቻ፣ደደር፣ኩርፋጨሌና መልካቦሎ በተባሉ ወረዳዎች የካዳስተር ሥራ ተግባራዊ እየሆነ ይገኛል።
በኢትዮጵያ የካዳስተር ሥራ ተቀባይነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱንም በፌዴራል የመሬት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ትዕግስቱ ገብረመስቀል ተናግረዋል።
በኦሮሚያ ክልል የካልም (CALM) ፕሮጀክት አስተባባሪ ታደለ ጫላ በበኩላቸው ÷የካዳስተር ሥራ የኅብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያሳደገው መምጣቱን ተናግረዋል፤ የካዳስተር ትግበራው የገጠሩን ማኅበረሰብ የቆየ ይዞታውን ወደ ህጋዊ መስመር እንዲያስገባ ታስቦ የተጀመረ መሆኑ ተገልጿል።
የምስራቅ ሐረርጌ ዞን የመሬት አስተዳደር ፅህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ጫልቱ አብዱረህማን ÷ የካዳስተር ሥራ ግጭቶችን እየቀነሰ መሆኑን ገልጸው፣ ቢሮው ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በሰራው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ አርሶ አደሩ መሬቱን በካዳስተር የማስመዝገብ ፍላጎቱም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል ነው ያሉት፡፡
የካዳስተር ሥራ ከዓለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ተግባራዊ እየሆነ እንደሚገኝም ነው የተመላከተው፡፡
በእዮናዳብ አንዱዓለም