የሀገር ውስጥ ዜና

የመዲናዋ ተማሪዎች፣ መምህራንና ፖሊሶች በሰንዳፋ ወረዳ የዘማች አርሶ አደሮችን የደረሰ ሰብል ሰበሰቡ

By Feven Bishaw

December 07, 2021

አዲስ አበባ፣ ህዳር 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የተመራው እና በከተማዋ የሚገኙ ተማሪዎችን፣ መምህራንና ፖሊሶችን ያካተተ ቡድን ዛሬ በሰንዳፋ ወረዳ የዘማች አርሶ አደሮችን የደረሰ የስንዴ ሰብል ሰበሰበ።

ከንቲባ አዳነች “የአዲስ አበባ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች፣ መምህራንና ፖሊሶች በሰንዳፋ ወረዳ በግራር በረክ ቀበሌ ህይወታቸውን ሳይሰስቱ ለሰጡ ጀግኖች ዘማች አርሶ አደሮችና የሚሊሻ ቤተሰቦች የደረሰ በ15 ሄክታር መሬት ላይ የነበረ የስንዴ ሰብል ሰብስበናል” ብለዋል።

የትምህርት ማህበረሰቡ ለህልውና ዘመቻው ደጀን እንዲሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ከህዳር 27 እስከ ታህሳስ 3 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ ዝግ እንዲሆን ትምህርት ሚኒስቴር መወሰኑ ይታወሳል።

በውሰኔው መሰረትም ትምህርት ዝግ በሚሆንበት ሳምንት መምህራንና ተማሪዎች አገርን በጋራ ለማቆም በሚደረገው ትግል ውስጥ የትምህርት ማህበረሰቡ ተሳትፎ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ተመልክቷል።

የትምህርት ማህበረሰቡ በሰብል መሰብሰብና በስንቅ ዝግጅት እንደሚሳተፍም ነው የተጠቆመው።

ይህንኑ ተከትሎ በአዲስ አበባ የዘማች ቤተሰቦችን ሰብል ለሚሰበስቡ 30 ሺህ የትምህርት ማህበረሰብ አባላት ትናንት ሽኝት መደረጉ ይታወሳል ፡፡

እነዚህ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች፣  መምህራንና የትምህርቱ ማህበረሰብ አካላት በከፍተኛ የሀገር ፍቅርና ወኔ የሚሳተፉበት ይህ የልማት ዘመቻ በቀጣይም ቀናት በደም ልገሳ፣ በአካባቢ ጥበቃና የዘማች አርሶ አደርና ሚሊሻዎችን የደረሰ ሰብል በመሰብሰብ የሚቀጥል መሆኑን ወይዘሮ አዳነች አቤቤ አስታውቀዋል ።