የሀገር ውስጥ ዜና

በተለያዩ አህጉራዊ እና አለም አቀፋዊ መድረኮች ላይ የኢትጵያን አቋም የሚያንፀባርቁ መልዕክቶች ተላልፈዋል

By Feven Bishaw

December 08, 2021

አዲስ አበባ፣ ህዳር 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በተለያዩ አህጉራዊ እና አለምአቀፋዊ መድረኮች ላይ የኢትዮጵያን አቋም የሚያንፀባርቁ መልዕክቶች ማስተላለፍ መቻሉን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ገለፀ፡፡

የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በሌላ በኩል ከሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ አቶ ከበደ ዴሲሳ በሰጡት መግለጫ፤ የህወሓት የሽብር ቡድን ወረራ ባካሄደባቸው አከባቢዎች ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈፅሟል፤ ንብረትና መሰረተ ልማቶች አውድሟል ብለዋል፡፡

ነገር ግን የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች ነን ባዮች፥ የሽብር ቡድኑ የፈጸማቸውን ኢሰብዓዊ ድርጊቶች ማንሳት አይፈልጉም፣ አሁንም በዝምታ ማለፍ መርጠዋል ነው ያሉት፡፡

በተቃራኒው መንግስት የሰብዓዊ መብት እንደጣሰ አድርገው ክስ ማቅረባቸውን ቀጥለዋል ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታው፡፡

እንዲሁም በአካባቢው እርዳታ የሚሹ የተፈናቀሉ ዜጎች እንዳሉ የገለፁት ሚኒስትር ዴኤታው፥ መንግስት የረድኤት ድርጅቶች ለተረጂ ወገኖች እርዳታ የሚያደርጉበትን መንገድ እያመቸቸ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በሌላ በኩል በአሜሪካ “በትግራይ የዘር ማጥፋት ተፈፅሟል” በሚል ኢትዮጵያን ለመወንጀል ለወራት ሲዘጋጅ የነበረው ረቂቅ አዋጅ በሀገሪቱ ብሄራዊ መከላከያ ፍቃድ ህግ መሰረዙን ሚኒስትር ዴኤታው አንስተዋል። ይህ ሰነድ ህግ ሆኖ እንዲፀድቅ የፈለጉ ወገኖችም ለወታደራዊ ጣልቃ ገብነት የህግ መሰረት ለመሰጠት አስበው እንደነበር ነው ያመለከቱት።

ሆኖም ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጅ ሀገራትና ዜጎች ግፊት ማድረጋቸውን ተከትሎ ሰነዱ ሳይፀደቅ ተሰርዟል። ለዚህም አበርክቷቸው ምስጋና አቅርበዋል።

በፌቨን ቢሻው