አዲስ አበባ፣ ህዳር 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሸባሪው ህወሓት ተወረው በነበሩ አካባቢዎች በቀጣይ ተፈናቃዮችን ወደቀያቸው የመመለስ ስራ እንደሚሰራ ተመለከተ።
የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽነር ዘላለም ልጅዓለም እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ሂክማ ከይረዲን ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ በማሕበራዊ ግንባር ዘርፍ ላይ ተወያይተዋል፡፡
ኃላፊዎቹ ከፋና ቴሌቪዥን ‹‹ስለኢትዮጵያ›› ዝግጅት ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ ህወሓት በአማራ እና በአፋር ክልሎች በሰው ልጆች ላይ በተለይም በህጻናትና በሴቶች እንዲሁም በመንግስትም ሆነ በህዝብ ንብረት ላይ ከፍኛ ጉዳት አድርሷል ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ሂክማ ከይረዲን፥ በተለይ በሴቶች ላይ የደረሱ በደሎች ስነ ልቦናዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳታቸው የጎላ በመሆኑ እነዚህን ችግሮች ለማስተካከል ከተማ አስተዳደሩ በትኩረት ይሠራል ብለዋል፡፡
እንደመንግሥትም ሆነ እንደከተማዋ ማህበረሰብ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በሽብር ቡድኑ በደረሰው ጥፋት ምክንያት የተጎዱ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም እንደሚሰራ አብራርተዋል፡፡
ለዚህም በተለያዩ ግንባሮች ለሚዋደቁ ጀግኖች እና ለተፈናቀሉ ወገኖች ከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ጠቁመው፥ ይህ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
በቀጣይ ከተማ አስተዳደሩ የኑሮ ውድነቱን በማረጋጋት፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ በመስጠት እና ኅብረ ብሔራዊ ዘመቻውን በመደገፍ ረገድ በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት፡፡
የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽነር ዘላለም ልጅዓለም በበኩላቸው፥ አሸባሪው ህወሓት በያዛቸው አካባቢዎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ድጋፍ ባለማድረጋቸው በምግብና በመድኃኒት እጥረት የብዙዎች ህይወት ማለፉን ገልጸዋል፡፡
በአማራ ክልል ህወሓት በቃለት የማይገለጽ ዘግናኝ ግፍ መፈጸሙን ጠቁመው፥ የደረሱ ቀውሶችን ለማስተካከል ክልሉ ዕቅድ መንደፉንም አስታውቀዋል፡፡
ለመልሶ ማቋቋም ሥራውም ባለሀብቶች፣ በሀገር ውስጥ እና በውጭ የሚኖሩ ሀገር ወዳዶች እንዲሁም የተለያዩ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘም የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሀ ግብሮች እንደሚኖሩ ጠቁመዋል፡፡
ለኅብረ ብሔራዊ ዘመቻው ኢትዮጵያውያን እያደረጉት ያለው ድጋፍ የሚደነቅ መሆኑን የገለጹት ኮሚሽነሩ፥ ይህም ሽብርተኛው ህወሓት በኢትዮጵያ መከፋፈልን እና ልዩነትን ለመትከል ያደረገው ጥረት እንዳልተሳከለት ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
የዘማች ቤተሰቦችንና ተፈናቃዮችን የመንከባከብ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፥ ለዚህም መንግሥታዊ ያልሆኑና መንግሥታዊ ተቋማት እያደረጉት ያለው ድጋፍ አበረታች ነው ብለዋል፡፡
በቀጣይ ተፈናቃዮችን ወደቀያቸው የመመለስ፣ መልሶ የማቋቋም እንዲሁም በክልሉ አሸባሪው ህወሓት የፈጸማቸውን አረመኔያው ድርጊቶች ለዓለም ዐቀፉ ማሕበረሰብ ለማሳወቅ እንሰራለን ብለዋል፡፡
በዩሀንስ ደርበው
አካባቢዎን ይጠብቁ! ወደ ግንባር ይዝመቱ! መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!