አዲስ አበባ ፣ ህዳር 30 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የልዩ ዘመቻዎች ሀይል፣ የሪፐብሊክ ጥበቃ ሀይል እና የአየር ወለድ አባላት በጭንቅ ላይ ያለች አገርን ችግር የፈቱ መሆናቸውን የመከላከያ የሰራዊት ግንባታ ስራዎች ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌ ገለጹ፡፡
ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌ ይህንን የተናገሩት የመጀመሪያውን ምዕራፍ የሽብር ቡድኑን የመደምሰስ ግዳጅ በድል መገባደድ እና ለቀጣይ ወሳኝ ተልዕኮ መነቃቃትን ለመፍጠር በሚያስችል መልኩ በግንባር በተካሄደ መድረክ ላይ በመገኘት ነው።
ቀይ መለዮ ለባሾቹ በወሳኝ ወቅት አስቸጋሪና ፈታኝ ግዳጆችን በድል በመወጣት በደማቅ ቀለም የተፃፈ ታሪክ መስራታቸውን ተናግረዋል።
ጀግኖቹ ከሰሞኑ በጣርማበርና ዙሪያ ገባዎቹ የፈፀሙት አንፀባራቂ ድል የጠላትን ቅስም የሰበረ ነው ያሉት ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌ፥ አሁንም የደም፣ የመስዋዕትነት እና የድል አድራጊነት ምልክት የሆነውን ቀይ መለዮአቸውን አጥልቀው ለዳግም ድል መትጋት እንዳለባቸው አሳስበዋል።