የሀገር ውስጥ ዜና

በአዲስ አበባ በአሸባሪው ህወሓት ለከፋ ችግር ለተጋለጡ ወገኖች በሁለት ሳምንት ውስጥ ከ240 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ ተደረገ

By Amare Asrat

December 09, 2021

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 30 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አዳነች አቤቤ በመዲናዋ በአሸባሪው ህወሓት ለከፋ ችግር ለተጋለጡ ወገኖች በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከ240 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ መደረጉን ገለጹ፡፡

በከተማ አስተዳደሩ ከማዕከል እስከ ክፍለ ከተሞች፣ ከነዋሪዎች እስከ ባለሀብቶች፣ አርሶ አደሮች፣ የሀይማኖት ተቋማት እና የሲቪክ ማህበራት፣ የተለያዩ የወጣቶች አደረጃጀቶች፣ የመንግስትና የግል ትምህርት ቤት ተማሪዎች አንዲሁም ሌሎች አደረጃጀቶች አማካኝነት ለህልውና ዘመቻው ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡

ነዋሪዎች ከትርፋቸው ሳይሆን ካለቻቸው እየቆረሱ በአሸባሪው ህወሓት ጥቃት ለከፋ ችግር ለተጋለጡ ወገኖቻችን፣ ለአገር መከላከያ እና ለፀጥታ ሀይሎቻችን በየግንባሩ ለሚገኙ ድጋፍ አድርገዋል ብለዋል፡፡

የጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች በአካል በመገኘት የሚያደርጉት ከፍተኛ ህዝባዊ ደጀንነት የታየበት ታሪካዊ ድጋፍ አሁንም ድረስ መቀጠሉን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ አስታውቀዋል።

ከንቲባዋ በቀረበው አገራዊ ጥሪ ወደኋላ ሳይሉ ለተሳተፉ አካላትም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።