የሀገር ውስጥ ዜና

በብሪታንያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ3 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ

By Meseret Awoke

December 10, 2021

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በብሪታንያ፣ በሊድስ ከተማና አካባባቢዋ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ3 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ አስረከቡ፡፡

ድጋፉ በአሻባሪው የህወሓት ወራሪ ሀይል ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች “እኔ እያለሁ ወገኔ አይራብም” በሚል መሪ ቃል ያሰባሰቡትን ድጋፍ ለንደን ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስረክበዋል፡፡

በለንደን የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈሪ መለሰ በርክክብ ስነ-ስርአቱ እንደተናገሩት ፥ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያ ላይ እየተካሄደ ያለውን ያልተገባ የውጭ ጫናን በመቃወም በልዩ ልዩ ከተሞች ያካሄዱት ሰላማዊ ሰልፍ የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን ለተፈናቀሉ ወገኖች አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ረገድ ያሳዩት ከፍተኛ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያውያኑ አገራቸው ያቀረበችውን የድጋፍ ጥሪ ተከትሎ በመላው ብሪታንያ ባለፉት ወራት አቅማቸው በፈቀደ ያከናወኑት የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት እጅግ የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡

በሊድስ ከተማና አካባቢዋ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በመወከል ገቢውን ያስረከቡት የማህበረሰቡ ተወካዮች በበኩላቸው ÷ ‘’ከእንግዲህ የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን ለመደገፍ በሚደረገው ማንኛውም ጥሪ የበኩላችንን ለማድረግ ዝግጁ ነን’’ ብለዋል፡፡

በቀጣይ የተለያዩ ዝግጅቶችን በማሰናዳት ገቢ እንደሚያሰባስቡም ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ሁለት ወራት በለንደን፣ በርሚንግሃም፣ ማንቸስተር፣ ኮቨንተሪ፣ ስቶክ ኦን ትሬንት ከተሞች በተዘጋጁ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅቶች ከ350 ሺህ ፓውንድ በላይ ገቢ መሰብሰቡን አምባሳደር ተፈሪ መለሰ ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ በመጪው ቅዳሜ ከ1 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሚሳተፉበት የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመደገፍ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት የሚካሄድ መሆኑን አምባሳደር ተፈሪ መለሰ መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በተመሳሳይ ናይሮቢ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አባላት በትናንትናው እለት ለተፈናቀሉ ወገኖች ሰብዓዊ ዕርዳታ የሚውል 23 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ድጋፍ አድርገዋል።

የገንዘብ ድጋፉን ተወካያቸው ኢንጂነር መስፈን እጅጉ ተፈራ በኤምባሲው ተገኝተው በኬንያ የኢፌዲሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር መለስ ዓለም ማስረከባቸውን ኢዜአ ዘግቧል ።

አካባቢዎን ይጠብቁ! ወደ ግንባር ይዝመቱ! መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!