አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ስለሰላም፣ ስለሀገራዊ ጥቅምና ስለብሄራዊ መግባባት ማጥናትና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን መጠቆም ከምሁራን እንደሚጠበቅ የሰላም ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደአ ገለጹ።
አቶ ታዬ ይህንን ያሉት በጅማ ዩኒቨርስቲ “የውጭ ተፅዕኖ እና የዩኒቨርስቲ ሚና” በሚል ርዕሰ በተዘጋጀ የምክክር መድረክ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ነው።
በመድረኩ ላይ ከዘጠኝ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ምሁራንና ተማሪዎች የተሳተፉ ሲሆን ፥ “የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሀገር ግንባታ እና የውጭ ተፅዕኖን የመቋቋም ሚና” የሚል ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደአ እንደተናገሩት ፥ ስለ ሰላም፣ ስለሃገራዊ ጥቅምና ስለብሄራዊ መግባባት በማጥናትና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በመጠቆም ረገድ የምሁራን ሚና የላቀ ነው።
ከሰብአዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘም በኢትዮጵያ ላይ የተዛባ መረጃ የሚያሰራጩ የምዕራባውያን ተቋማት፥ አሸባሪው ህወሃት ለ27 ዓመታት በዜጎች ላይ ኢ-ሰብአዊ የጭካኔ ተግባር ሲፈፅም በዝምታ ሲያልፉ ነበር ብለዋል።
ነገር ግን አሁን ላይ በኢትዮጵያ የህዝብና የሀገር ጥቅም የሚያስቀድም ጠንካራ መንግስት መመስረቱ ስጋት የፈጠረባቸው እነዚህ አካላት የተለያዩ ጫናዎችን ለማሳደር እየጣሩ መሆኑንም ነው አቶ ታየ የገለጹት።
በመሆኑም ይህ ዓይነቱን ጫና በመቀልበስና ሀገራዊ መግባባትን በመፍጠር ረገድ ምሁራን ጉልህ ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባ አቶ ታዬ ጠቁመዋል።
በሙክታር ጣሃ
አካባቢዎን ይጠብቁ! ወደ ግንባር ይዝመቱ! መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!