አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በምስራቅ ሸዋ ዞን ጉምብቹ ወረዳ በ331 ሄክታር መሬት ላይ የተዘራ የዘማች ቤተሰቦች ሰብል በተማሪዎች መሰብሰቡን የምስራቅ ሸዋ ዞን ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቶሌራ ዋሚ አስታወቁ፡፡
የዘማች ቤተሰቦቹ ሰብል የተሰበሰበው ከሶስት 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በተውጣጡ 1 ሺህ 895 ተማሪዎች ሲሆን፥ የተከናወነው ሥራ በገንዘብ ሲተመን ከ5 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር በላይ ግምት እንዳለውም ነው የተገለጸው፡፡
ተማሪዎቹ ሰብል በመሰብሰብ በአገራቸው ጉዳይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እንዲሳተፉ መንግስት ጥሪ በማድረጉ መደሰታቸውን ተናግረዋል።
መማርም ሆነ በሰላም ወጥቶ መግባት የሚቻለው አገር ሰላም ስትሆን በመሆኑ፥ ከዚህም በላይ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን አስረድተዋል፡፡
የዘማች ቤተሰቦችም አገርን ከጠላት ለመከላከል ወደ ግንባር የዘመቱ ቤተሰቦቻቸው የዘሩትን ሰብል ተማሪዎች በመሰብሰባቸው እንተደሰቱ መናገራቸውን ከትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
አካባቢዎን ይጠብቁ! ወደ ግንባር ይዝመቱ! መከላከያን ይደግፉ!