የሀገር ውስጥ ዜና

አዲስ አበባ የበርካታ ሀገራት አምባሳደሮችንና ዲፕሎማቶችን ያሰባሰበ ዓውደ ርዕይ አሥተናግዳለች

By Alemayehu Geremew

December 11, 2021

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የባንግላዴሽ ኤምባሲ ከሀገር ውስጥ የጥበብ ሰዎች ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የሥዕል አውደ ርዕይ ላይ ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ የሆኑ የበርካታ ሀገራት አምባሳደሮች ታዳሚ ሆነዋል።

በአውደ ርዕዩ ላይ በሀገራችን ሠዓሊዎች የተሣሉ በርካታ የጥበብ ሥራዎች እና የኢትዮጵያንና የባንግላዴሽን ባሕል እና ታሪክ የሚያንጸባርቁ ልዩ ልዩ የጥበብ ሥራዎች ቀርበዋል፡፡

የኢራን፣ ሳኡዲ አረቢያ፣ ሉክዘምበርግ፣ ኖርዌይ፣ የፊንላንድ፣ ሰሜን ኮሪያ፣ ባንግላዴሽ፣ ሩሲያ፣ አውስትራሊያ፣ ቬንዙዌላ እና ቼክ ሪፐብሊክ አምባሳደሮች እንዲሁም የበርካታ ሀገራት ዲፕሎማቶች በዓውደ ርዕዩ ላይ ተካፍለዋል፡፡

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያነጋገራቸው የሀገራት አምባሳደሮች እንደተናገሩት፥ ዓውደ ርዕዩ የኢትዮጵያን ምስል ለዓለም ያስተዋወቀ እና በቀጣይ ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገራት ጋር በምታደርገው የባሕል እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ምቹ ዐውድ የፈጠረ ነው ብለዋል፡፡

ዓውደ ርዕዩ መዘጋጀቱ የዲፕሎማቶች እና የአምባሳደሮች መቀመጫ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ እንደ ወትሮው ሁሉ ሠላም እንደሆነች እና የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎችም እንደቀጠሉ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚያሳይ ነውም ተብሏል፡፡

በኢትዮጵያና በዓለም ዙሪያ ያሉ የጥበብ ሰዎችም የሥነ ጥበብ ምልከታቸውን እርስ በእርስ እና ለዓለም እንዲያካፍሉ ይህን መሰል ዓውደ ርዕዮች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ተብሏል፡፡

በኢትዮጵያ የባንግላዴሽ አምባሳደር ናዝሩል ኢስላም ÷ የሀገራቸው የጥበብ ሥራዎች እና የኢትጵያን ባሕል እና ታሪክ የሚያንጸባርቁ የሥዕል ሥራዎች ለተቀረው የዓለም ክፍል የሚቀርቡበት መርሃ ግብር በቀጣይ የሚዘጋጅበትን ሁኔታም እናመቻቻለን ነው ያሉት፡፡

በወንድወሰን አረጋኸኝ