አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል የተለያዩ ዞኖች አሸባሪው ህወሓት በሴቶችና ህፃናት ላይ እያደረሰ ያለውን ጥቃት የሚያወግዙ ሰልፎች ተካሄዱ፡፡
በደቡብ ክልል በጉራጌ ፥ በስልጤ እና በከምባታ ጠምባሮ ዞኖች ነው “ሠላም ይስፈን፤ በሕፃናትና ሴቶች ላይ የሚፈፀም ጥቃት ይብቃ” በሚል መሪ ቃል የሽብር ቡድኑን የሚያወግዙ የሴቶች የተቃውሞ ሰልፎች የተካሄዱት።
“ሰላም ይስፈን በሴቶችና ህፃናት ላይ ጥቃት ይቁም!” በሚል መሪ ቃል በጉራጌ ዞን በወልቂጤ ከተማ በተካሄደው ሰልፍ፥ አሸባሪው ህወሓት በሴቶችና ህፃናት ላይ ያደርሰውንና አሁንም እያደረሰ ያለውን ጥቃት ሰልፈኞቹ በጥብቅ አውግዘዋል።
አውግ ጥቃት ታሪክ ይቅር የማይለው በመሆኑ እኩይ ድርጊቱን የሚያወግዝና የውጭ ጣልቃ ገብነት እንዲቆም የሚጠይቅ ዞን አቀፍ የሴቶች የተቃውሞ ሰልፍ እያካሄዱ ነው።
የከምባታ ጠምባሮ ዞን ሴቶች አሸባሪው የትህነግ ቡድን በሕፃናትና ሴቶች ላይ እያደረሰ ያለውን ጥቃት የሚያወግዝ ሰልፍ በዱራሜ ከተማ ተካሂዷል።
በተመሳሳይ በስልጤ ዞን በሁሉም ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የሚገኙ ሴቶች አንዳንድ ምዕራባውያን መንግስታት በኢትዮጵያ ላይ እያደረጉት ያለውን ጣልቃ ገብነትና አሸባሪው ቡድን በሴቶችና ህፃናት የሚፈጽመውን ግፍና በደል የሚያውግዙ እና መከላከያ ሠራዊትን የሚደግፉ መፈክሮችን በማሰማት ነው ሰልፎች በተለያዩ ከተሞች የተካሄዱት።
በተጨማሪም በሀላባ የአሸባሪውን ህወሓት እኩይ ተግባር የሚያወግዝ የሴቶች የጎዳና ላይ ሰልፍ ተካሂዷል።
አሸባሪው ቡድን በኢትዮጵያ በተለይም በአማራና አፋር ክልሎች በከፈተው ጦርነት የመጀመሪያው ገፈት ቀማሽ የሆኑት ሴቶችና ህጻናት በመሆናቸው ነው የሽብር ቡድኑን እኩይ ተግባር የሚያወግዝ ሰልፍ የተካሄደው።
በክልሉ የተለያዩ ዞኖች ሴቶች ‘‘አገራችን የገጠማትን የህልውና ጦርነት ለመዋጋት ከአገር መከላከያ ጎን ነን፣ ለሀገር መከላከያ ስንቅ ከማዘጋጀት ጀምሮ ልጆቻችን ወደ ግንባር በመላክ ለሀገራችን ደጀን እንቆማለን፤ የውጭ አገር ጣልቃ ገብነት በቃ ፤ ሰላም ይስፈን በሴቶችና ህፃናት ላይ ጥቃት ይቁም፤ ሴቶች ጀግና እንወልዳለን ፣ ጀግና እናዘምታለን ፤ እኛም እንዘምታለን ፤ መሪዋ ለዘመተላት አገር እኔም አለሁላት’’ የሚሉና መሰል መፈክሮችን አሰምተዋል።
ምንጭ ፡- የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮና የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት።
አካባቢዎን ይጠብቁ! ወደ ግንባር ይዝመቱ! መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!