የሀገር ውስጥ ዜና

ዳያስፖራው ወደ አገር ቤት ለመምጣት ከፍተኛ ተነሳሽነት እያሳየ ነው

By Meseret Awoke

December 14, 2021

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተከትሎ ዳያስፖራው ወደ አገር ቤት ለመምጣት ከፍተኛ ተነሳሽነት እያሳየ መሆኑን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በውጭ አገራት የሚኖሩ 1 ሚሊየን ኢትዮጵያውያንና ትውልደ -ኢትዮጵያውያን ለመጪው ገና ወደ አገር ቤት እንዲመጡ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡

ወደ አገር ቤት ሲመጡ ደግሞ እያንዳንዳቸው አንድ የውጭ አገር ዜጋ ይዘው እንዲመጡ ጥሪ መቅረቡም ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ወንድወሰን ግርማ ለኢዜአ እንደተናገሩት ÷ ጥሪውን ተከትሎ ዳያስፖራው ወደ አገር ቤት እንዲመጣ ኤጀንሲው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እቅድ አውጥቶ በቅንጅት እየሰራ ነው፡፡

ጉዳዩን የሚያስተባብር ብሔራዊ ኮሚቴ መቋቋሙን ገልጸው ÷ በተለያዩ አገራት ያሉ የኢትዮጵያ ሚሲዮኖች ዳያስፖራው ወደ አገር ቤት እንዲመጣ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ዳያስፖራው በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለውን ያልተገባ የውጭ ጣልቃ ገብነት በመቃወም የ “በቃ” ዘመቻ ሲያካሂድ መቆየቱን አስታውሰው ÷ የዘመቻው አካል የሆኑ ሰልፎች በ40 የተለያዩ ከተሞች መካሄዳቸውን ገልጸዋል፡፡

“አንዳንድ የውጭ አገራት ኢትዮጵያ ሰላም እንዳልሆነች በማስመሰል ዜጎቻቸውን ለማስወጣት ጥሪ ሲያቀርቡ እየተሰማ ነው” ያሉት አቶ ወንድወሰን ÷ ከዚህ አኳያ የዳያስፖራው ወደ ኢትዮጵያ መምጣት አንዳንድ የምዕራባውያን ሚዲያዎች ኢትዮጵያን በሚመለከት የሚያሰራጩት መረጃ ትክክል አለመሆኑን እንደሚያጋልጥም ነው የተናገሩት፡፡

ዳያስፖራው በምዕራባውያን ዘንድ ከፍተኛ ወጪ የሚወጣበትን የገና በዓል በኢትዮጵያ ማሳለፉ ደግሞ የአገር ውስጥ ቱሪዝምንና የአገልግሎት ሰጪ ዘርፉን የሚያነቃቃ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኤጀንሲው ዳያስፖራው በችግር ውስጥ የሚገኙ ወገኖቹን የሚደግፍበት “አይዞን ዶት ኮም” የተሰኘ የድረ ገጽ መተግበሪያ ማዘጋጀቱን ገልጸው÷ በተለይ የ”#በቃ” ዘመቻ ከተጀመረ ወዲህ መተግበሪያውን በመጠቀም ድጋፍ የሚያደርጉ የዳያስፖራ አባላት ቁጥር ጨምሯል ነው ያሉት፡፡

አካባቢዎን ይጠብቁ! ወደ ግንባር ይዝመቱ! መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!