ዓለምአቀፋዊ ዜና

ቻይናና ፈረንሳይ የታዳጊ አገራትን የዕዳ ጫና ለማቃለል በጋራ ሊሰሩ ነው

By Meseret Awoke

December 14, 2021

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና እና ፈረንሣይ ባደረጉት መደበኛ የሁለትዮሽ ስብሰባ ለአካባቢ ጥበቃ ተስማሚ የኢኮኖሚ ልማት ትብብር ለማድረግ፣ ታዳጊ አገራትን ለመደገፍ እና የኮቪድ-19 ወረርሽኝን በጋራ ለመዋጋት ተስማምተዋል።

በውይይቱ ወቅት አገራቱ በታዳጊ አገሮች ላይ ያለውን የዕዳ ጫና ለማቃለል በጋራ እንደሚሰሩ መናገራቸው በዘገባው ተጠቅሷል ፡፡

በበይነ መረብ የተካሄደውን የሁለቱ ሀገራት ስምንተኛው ከፍተኛ የኢኮኖሚ እና የፋይናንስ ውይይት የቻይናው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሁ ቹንዋ እና የፈረንሣይ ምጣኔ ሃብት እና ፋይናንስ ሚኒስትር ብሩኖ ለሜሬ መርተውታል፡፡

ሁለቱ አገራት ታዳጊ አገሮችን ለመደገፍ እየሰሩ ያሉት ስራም ጥሩ ውጤት ማስመዝገቡን የገለጹት የቻይናው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር በቀጣይም በተጠናከረ መልኩ በጋራ እንደሚሰሩ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

በአገራቱ መሪዎች ጠንካራ አመራርነት በቻይና እና በፈረንሳይ መካከል ያለው የቅንጅት ስራ አወንታዊ እድገት አሳይቷል ያሉት ሁ ቹንዋ፥ የሁለትዮሽ ንግድ ግንኙነቱም ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን እና የአገራቱ ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በፍጥነት ማደጉን ገልጸዋል፡፡

ከዚህም ባለፈ ሁለቱ ሀገራት በተለያዩ ቁልፍ በሆኑ እና የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያመጡ ጉዳዮች ላይ ትብብራቸውን ለመቀጠል መዘጋጀታቸውንም ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ አስገንዝበዋል።

የፈረንሳይ ምጣኔ ሃብት እና የፋይናንስ ሚኒስትር ለ ማይሬ በበኩላቸው ፈረንሳይ ለሁለትዮሽ ግንኙነት ትልቅ ቦታ እንደምትሰጥ ገልፀው ከቻይና ጋር በኢኮኖሚ እና በፋይናነስ ጉዳዮች የበለጠ ለመተባበር ፈቃደኛ መሆኗን ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ፣ በብዝሀ ሕይወት ጥበቃ እና የዓለም ንግድ ድርጅት ማሻሻያዎችን ጨምሮ በሌሎች አበይት ጉዳዮች ላይ በጋራ በመስራት ፈረንሳይ ከቻይና ጋር ያላትን ግንኙነት እና ትብብር ለማጠናከር ዝግጁ ናት ማለታቸውንም ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡

በአመለወርቅ ደምሰው

አካባቢዎን ይጠብቁ! ወደ ግንባር ይዝመቱ! መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!