ዓለምአቀፋዊ ዜና

የቻይና እና የሩሲያ ግንኙነት የዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሳሌ

By Alemayehu Geremew

December 16, 2021

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 7 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ስርጭት እየተስፋፋ ባለበት በዚህ ወቅት የሩሲያ እና የቻይና ግንኙነት ወረርሽኙን በጋራ በመከላከል እና በሌሎች የትብብር መስኮች ይበልጥ እየተጠናከረ መምጣቱ ተገለጸ፡፡

የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ እና የሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን በበይነ መረብ ባካሄዱት ውይይት ÷ ሁለቱ ሀገራት ሁሉን አቀፍ በሆነ የትብብር መስኮች ለመሥራት መነሳሳታቸውን አመላክተዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ጂንፒንግ ሀገራቸው ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር በምታደርገው ጥረት ሩሲያ ያሳየችውን ድጋፍ አድንቀዋል፡፡

በሁለቱ ሀገራት መካከል ምንም አይነት አሉታዊ ጣልቃ ገብነት እንዲኖር ቻይና እንደማትፈቅድም ነው የተናገሩት፡፡

የቻይና እና የሩሲያ የመልካም ጉርብትና እና ወዳጃዊ የትብብር ስምምነት የተፈረመበት 20ኛ ዓመት መከበሩን ፕሬዚዳንት ሺ አስታውሰው ፥ ሀገራቱ ስምምነቱን ለተጨማሪ 5 ዓመታት ለማራዘም መወሰናቸውንም ነው የገለጹት፡፡

ሁለቱ ሀገራት በጋራ ተጠቃሚነት ላይ በትብብር እንደሚሰሩና እርስ በእርስ በመረዳዳት ብሔራዊ ክብራቸውን እንደማያስደፍሩም አውስተዋል፡፡

በፈረንጆቹ 2021 በሁለቱ ሀገራት መካከል ጠንካራ የፖለቲካ ግንኙነት እንደተፈጠረና በንግዱ ዘርፍም በመጀመሪያዎቹ ሶስት ሩብ ዓመታት ለመጀመሪያ ጊዜ የ100 ቢሊየን ዶላር ግብይት በመፈጸም ከመቼውም ጊዜ በላይ ጠንካራ የተባለለት የንግድ ትስስር መፍጠር እንደቻሉም ነው የተመላከተው፡፡

ሀገራቱ በቀጣይ በሣይንስ እና ቴክኖሎጂ ፈጠራዎች፣ በቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ፣ በታዳሽ ኃይል፣ በኒውክሌር ኃይል እና የኮቪድ 19 ወረርሽኝን በጋራ በመከላከል ላይ ስትራቴጂ ቀርጸው እንደሚሰሩ አስረድተዋል።

በተባበሩት መንግስታት የታቀደውን የ2030 ቀጣይነት ያለው እድገት አጀንዳ ለማረጋገጥም ሩሲያ እና ቻይና በጋራ እንደሚሰሩ ነው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ የተናገሩት፡፡

ሁለቱ ሀገራት ግንኙነታቸውን “የ21ኛው ክፍለ ዘመን የዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሳሌ” ሲሉም ማሞካሸታቸውን ሲ ጂ ቲ ኤን ዘግቧል፡፡