አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ እና ተጠሪ ተቋማት ለመከላከያ ሠራዊት እና በጦርነቱ ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ44 ሚሊየን ብር በላይ በዓይነትና በገንዘብ በደሴ ግንባር ተገኝተው ድጋፍ አድርገዋል።
የምግብ፣ የአልባሳት፣ የንፅህና መጠበቂያ፣ የህፃናት ምግብ እና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ያካተተ በዓይነት እና በገንዘብ ድጋፍ ተደርጓል።
በድጋፍ ርክክቡ ላይ የተገኙት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አካሉ አሰፋ እንደተናገሩት፥ አሸባሪው ህወሓት በወገናችን ላይ ያደረሰውን ችግር ለመቅረፍ የቢሮውና ተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ሠራተኞች ሁለንተናዊ ድጋፍ በማድረግ የበኩላችንን ሚና እየተወጣን ነው ብለዋል።
ሁለንተናዊ ድጋፉ ተጠናክሮ መቀጠሉን የጠቀሱት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፥ መከላከያን ከመደገፍ ጎን ለጎን በጦርነቱ ለተጎዱ የአካባቢው ነዎሪ ወገኖቻችንም ልንደርስላቸው ይገባል ብለዋል።
በዚህ ረገድ የቢሮውና የተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ሠራተኞች ገንዘብ በማዋጣት፣ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት፣ አልባሳትንና የተለያዩ ምግብና ምግብ ነክ አቅርቦቶችን በመግዛት በድምሩ 44 ሚሊየን 75 ሺህ 359 ብር የሚሆን ድጋፍ መደረጉን ገልፀዋል።
አያይዘውም፥ እየተደረገ ካለው የገንዘብ፣ የጉልበትና መሰል ድጋፍ ባሻገር ጠላትን ለመደምሰስ በሚደረገው ትግል ሠራተኞቻችን ጭምር በግንባር በመዝመት የህይወት መሰዋዕትነት ለመክፈል መሰለፋቸውን አስታውቀዋል።
ሁለንተናዊ ድጋፉን አጠናክረን እንቀጥላለን ያሉት አቶ አካሉ ከመከላከያና ከተፈናቃይ ወገኖቻችን ጎን መሆናችንን ዛሬም ነገም እናረጋግጣለን ብለዋል።
በሀብት አሰባሰቡም ቢሮው እና በስሩ የሚገኙ የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ፣ አሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን፣ አንበሳ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት እና ሸገር የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት አመራሮችና ሠራተኞች ድርሻቸውን አበርክተዋል።
ድጋፉም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ እና ተጠሪ ተቋማት አመራሮች በኩል በደሴ ግንባር ርክክብ መደረጉን ከቢሮው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
አካባቢዎን ይጠብቁ! ወደ ግንባር ይዝመቱ! መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!