የሀገር ውስጥ ዜና

በሸካ ዞን የእርስ በእርስ ግጭት በማስነሳት የሰው ሕይወት እንዲጠፋ ያደረጉ 36 ግለሰቦች በፅኑ እስራት ተቀጡ

By Mekoya Hailemariam

December 23, 2021

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ)  በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሸካ ዞን የእርስ በእርስ ግጭት በማስነሳት የሰው ሕይወት እንዲጠፋና ከባድ የንብረት ውድመት እንዲደርስ ያደረጉ 36 ግለሰቦች ከ19 ዓመት እስከ 6 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራትና በገንዘብ እንዲቀጡ ተወሰነባቸው።

ተከሳሾች በወንጀል ህጉ የተመለከቱትን ድንጋጌዎች በመተላለፍ፥ አንዱ ወገን በሌላ ወገን ላይ ጦር መሳሪያ በማንሳት የእርስ በእረስ ጦርነት እንዲነሳ በማሰብ በቀድሞ በደቡብ ክልል ሸካ ዞን ዬኪ ወረዳ ቴፒ ከተማ እና አጎራባች ቀበሌዎች በሚገኙ አካባቢዎች ከሐምሌ 11 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት እራሳቸውን የሰላም ኮሚቴ በማለት ሕጋዊ መንገድን ባልተከተለ መልኩ በቡድን መደራጀታቸውን የክስ መዝገቡ ያነሳል።

ከወረዳ እስከ ቀበሌ ድርስ መዋቅራቸውን በመዘርጋት፤ በቴፒ ከተማ እና በአከባቢው የሚገኙ ቀበሌዎችን ህዝቦች በተለያየ ጊዜ እየሰበሰቡ በዞን የመደራጀት የመዋቅር ጥያቄያችን ሊመለስ ይገባል፤ እንዳይመለስ የሚያደርገው የሸካ ብሔር ነው ስለዚህ የሸካ ብሔር እና የሸካ ብሔር ደጋፊ ናቸው የሚሏቸውን የመንጅ እና የቤንች ብሔር ተወላጆች ላይ የሀይል እርምጃ መውሰድ አለብን በማለት ህዝቡ ለመንግስት መዋቅር ታዛዥ እንዳይሆን ማድረጋቸውንም ይዘረዝራል።

የመንግስትና የግል ድርጅቶች እንዲዘጉ፤ የማጓጓዣ አገልግሎት እንዲቋረጥ እና የሸካ፤ የመንጅ እና የቤንች ብሄር ተወላጆች ተለይተው የሞት እና የአካል ጉዳት እንዲደርስባቸው፤ ቤት ንብረታቸው እንዲወድም ፤ እንዲዘረፍ እና ከሚኖሩበት አካባቢ አንዲፈናቀሉ አነሳስተዋልም ይላል።

የጦር መሳሪያ ማለትም ክላሽ፣ ገጀራ፣ ጦር፣ ጩቤ፣ ድንጋይ እና ማንኛውም ሰውን ሊጎዳ የሚችል መሳሪያ በመያዝ የሸክቾ፣ የቤንች እና መንጅ ብሔር ተወላጆችን በመለየት እና ጥቃት በማድረስ የ33 ሰዎች ሕይወት አንዲያልፍ፣ ዘጠኝ  ሰዎች ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት እንዲደርስባቸው፣ 11 ሺህ 148 ዜጎች ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ፣ የ455 አባወራ መኖርያ ቤቶች እንዲቃጠሉ፣ 53 የመንግስትና የግል የጦር መሳርያ እንዲዘረፍና በአጠቃላይ ከ80 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት እንዲወድም ማድረጋቸውን የክስ መዝገቡ እንደሚዘረዝር ከፍትህ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ተከሳሾቹ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ በመሳተፍ በመንግስት ላይ በሚደረግ ወንጀል፣ በፈፀሙት ከባድ የሰው ግድያ፣ ከባድ በንብረት ላይ ጉዳት ማድረስ ፣ ነዳጅ በማርከፍከፍ እሳት ለኩሰው ቤትና ንብረት እንዲቃጠል በማድረግ በፈፀሙት ወንጀል በዋና ወንጀል እድራጊነት ተካፋይ በመሆናቸው በዐቃቤ ህግ ክስ ተመስርቶባቸውል።

በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሚዛን፣ ቦንጋ፣ ቴፒ፣ ጋምቤላና አካባቢው ተዘዋዋሪ ችሎት ጉዳዩን ሲመለከት ከቆየ በኋላ በዐቃቤ ህግ ክስ ከተመሰረተባቸው 51 ተከሳሾች ውስጥ በፖሊስ ያልቀረቡ፣ ምስክር ያልቀረበባቸውና በነፃ ከተሰናቱ ውጭ ቀሪ 36 ተከሳሾች ላይ ችሎቱ ታህሳስ 13 ቀን 2014 ዓ.ም በዋለው ችሎት የቅጣት ውሳኔ ሰጥቷል።

በዚህም መሰረት ማንይሁን ባትገኝ፣ ተመስገን ጀማል፣ መሰረት ወንድሙ፣ ዘማች ከይላና ሳሙዔል ካይቤንስ የተባሉት ተከሳሾች እያንዳንዳቸው በ19 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ሲወስንባቸው 2 ተከሳሾች እያንዳንዳቸው በ17 ዓመት ፅኑ እስራት፣ ቀሪ 29 ተከሳሾች ደግሞ እንደተከሰሱበት አንቀፅ ከ12 ዓመት ፅኑ እስራትና በ2 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት አንስቶ እስከ 6 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ተወስኖባቸዋል።