አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ ዜጎቿን አስገድዳ የምታሠራ ሀገር መሆኗን በቻይና የዢን ጂያንግ አስተዳደር ቃል-አቀባይ ዡ ጒይ ዢያንግ ገለጹ፡፡
ዡ ጒይ ዢያንግ ቤጂንግ በሠጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ÷ አሜሪካ በታሪኳ ለበርካታ መቶ ዓመታት በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ዜጎች ላይ በምታደርሰው በደል እንዲሁም በጥቁሮች ላይ በምትፈጽመው አድልዖ ትታወቃለችም ነው ያሉት፡፡
የአሜሪካ የግብርናው ዘርፍ ደግሞ ሀገሪቷ ዜጎቿ ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ከምትፈጽምባቸው ዘርፎች ውስጥ ዋነኛው መሆኑን ማንም አይክድም ሲሉ ቃል አቀባዩ ገልጸዋል፡፡
ቻይና በዜጎቿ ላይ ጫና ታሳድራለች፤ የሚለውንም የአሜሪካ ክስ ዡ አጣጥለው ÷ በዢንጂያንግ የሚኖሩ ዜጎቼ በየትኛውም ቦታ ተንቀሳቅሰው የመሥራት መብት አላቸው ብለዋል፤ ይልቁንም ቻይና ዜጎቿ የተሻለ ሕይወት እንዲኖሩ የሥራ ዕድሎችን ታመቻቻለችም ነው ያሉት፡፡
አሜሪካ እያደረገች ያለችው ሙከራ የዢን ጂያንግን ኢኮኖሚ ለማድቀቅ ያለመ ነውም ብለዋል፡፡
የአሜሪካ “የላብ-አደር ህግ” በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ ዜጎቿን ያላማከለ እና ለመሠረታዊ መብቶቻቸውም ከለላ የማይሰጥ ነው ብለዋል፡፡
30 በመቶ የሚሆኑ በአሜሪካ በግብርና የተሰማሩ ዜጎችም ከእነ ቤተሰቦቻቸው ከሀገሪቷ የድህነት ጣሪያ በታች እንደሚኖሩም ቃል-አቀባዩ ተናግረዋል፡፡
በአሜሪካ የሥራ ገበያ ውድድር ውስጥ አካል ጉዳተኞች እና ሴቶች ከተቀሩት ዜጎች እኩል መብታቸው እንደማይከበር እና አድልዖ እንደሚፈጸምባቸው ነው ቃል አቀባዩ የተናገሩት፤ በግለሰቦች በሚዘወር እስር ቤቶችም የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሚፈጸም መጠቆማቸውን ሲጂቲ ኤን ዘግቧል፡፡