የሀገር ውስጥ ዜና

በሪፎርሙ የዴሞክራሲ ስርዓት ለመገንባት በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል- አቶ ዛዲግ አብርሃ

By Meseret Awoke

December 29, 2021

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 20፣ 2014 (ኤፍ ቢሲ) በሪፎርሙ የዴሞክራሲ ስርዓት ለመገንባት በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል ሲሉ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሚኒስትር አቶ ዛዲግ አብርሃ ተናገሩ።

ሚኒስትሩ ከፋና ቴሌቪዥን “ዴሞክራታይዜሽን እና ህብረ ብሄራዊነት” በሚል ርዕስ በተካሄደው ስለ ኢትዮጵያ ፕሮግራም ላይ ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት፥ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ በአንድ ጊዜ የሚመጣ ሳይሆን በረዥም ጊዜ ልምምድ እና ትግበራ የሚበለፅግ ነው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሽግግር ከተደረገ በኋላ የዴሞክራሲ ስርዓት ለመገንባት በርካታ ስራዎች መከናወን መቻላቸውን አብራርተዋል፡፡

በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ የፖለቲካ አስረኞች ተፈተዋል፣ የሚዲያ ነፃነት ተከብሯል፣ የጸጥታ እና ሌሎች ተቋማት ከፖለቲካ ገለልተኛ እንዲሆኑም ተደርጓል ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡

ብሄራዊ መግባባትን ለማምጣት በገዢው ፓርቲ እና በተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል ያለውን ልዩነት ማጥበብ መቻሉን የገለጹት ሚኒስትሩ፥ ለዚህም ማሳያ የሚሆነው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ጋር ከአስር ጊዜ በላይ ስብሰባ ማድረጋቸውንና በዚህም ሰላማዊ እና በሃገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን ምርጫ ማካሄድ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በታዳጊ ሃገራት ላይ ዴሞክራሲ መገንባት እጅግ ከባድ ነው፤ ይሁን እንጂ አሁን ላይ ኢትዮጵያ አውነተኛ ሽግግር ላይ ትገኛለች ብለዋል፡፡

ዴሞክራሲ አውቅና ለማግኘት ሳይሆን አንድን ሃገር ወደ ልማት እና አድገት እንደትሻገር የሚያደርግ ነው ያሉት አቶ ዛዲግ፥ የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ስርዓት የሚተቹ ምዕራባውያን ሃገሪቱ ባደረገቸው ለውጥ ጥቅማቸው የተነካባቸው ናቸው ብለዋል፡፡

ምዕራባውያን በተለይም አሜሪካ የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ አቋም ከተረዳች በኋላ አሸባሪውን ህዋሃት ከመርዳት በተጨማሪ በኢትዮጵያ ላይ የተለያዩ ጫናዎችን እያደረገች መሆኑንም ሚኒስትሩ ገልፀዋል፡፡

ይሁን እንጂ በአሜሪካ የሚታገዘው ህዋሃት አሁን ላይ በሃገሪቱ ላይ ተፅዕኖ ለማድረስ ቀርቶ ራሱን የማይከላከልበት ደረጃ ላይ ደርሷል ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡

አካባቢዎን ይጠብቁ! ወደ ግንባር ይዝመቱ! መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!