አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 20 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሜሪካ እና በአውሮፓ በየቀኑ በኮሮና ቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑ ተገለጸ።
በቅርቡ የተከሰተው አዲሱ ኦሚክሮ የኮቪድ19 ቫይረስ የሚያዙ ሰዎችን ቁጥር ከፍ እንዳደረገውም ነው የተመላከተው።
በተለይ በአሜሪካ የቫይረሱ ስርጭት ከፍ በማለቱ በአንድ ቀን ብቻ 512 ሺህ 513 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ሲያዙ 1 ሺህ 762 ሰዎች ደግሞ ህይወታቸው ማለፉን የሃገሪቱ በሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል አስታውቋል።
ባለፈው ሳምንት በአሜሪካ 1 ሚሊየን 660 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸውን አጥተዋል ተብሏል፡፡
ማዕከሉ እንደገለጸው የሰባት ቀን አማካይ ዕለታዊ ጭማሪ ከ206 ሺህ በላይ የተመዘገበ ሲሆን ይህም ከፈረንጆች ጥር 18 ጀምሮ ከፍተኛው አሃዝ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡
መረጃው እንደሚያመላክተው በሀገሪቱ በከፍተኛ ሁኔታ እየተሰራጨ ካለው የኮሮና ስርጭት 58 ነጥብ 6 በመቶ የሚሆነው ኦሚክሮን ሲሆን፥ ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ ከፍተኛ ጫና ፈጥሮ የነበረው የዴልታ ቫይረስ ደግሞ 41 ነጥብ 1 በመቶ ድርሻ ይይዛል፡፡
የቫይረሱ ስርጭት በዚህ ሁኔታ ማሻቀብ በሀገሪቱ ሆስፒታሎች ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሯልም ነው የተባለው፡፡
በተመሳሳይ በአውሮፓም የቫይረሱ ስርጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መምጣቱ ተጠቁሟል።
ማክሰኞ እለት በፈረንሳይ 179 ሺህ 807 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ ይህም በአውሮፓ አህጉር በአንድ ቀን ውስጥ የተመዘገበ ከፍተኛው ቁጥር ሆኗል።
ከፈረንሳይ በተጨማሪም ብሪታንያ፣ ፖርቹጋል፣ ጣሊያን እና ግሪክ እንደሚገኙበት ሲ ጂ ቲ ኤን ዘግቧል፡፡