የሀገር ውስጥ ዜና

በደብረ ብርሃን የነበሩ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እየተመለሱ ነው

By Meseret Awoke

December 30, 2021

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከቀያቸው ተፈናቅለው በደብረብርሃን በ12 የመጠለያ ካምፖች ውስጥ ከሰፈሩ ተፈናቃዮች በዘጠኝ ካምፕ ውስጥ የነበሩ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ደበበ ዘውዴ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ በዘጠኝ ካምፖች ውስጥ ተጠልለው የነበሩት ከ455 ሺህ በላይ ዜጎች ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን ገልጸዋል፡፡

ተመላሾቹ ከደሴ፣ ኮምቦልቻ እንዲሁም ከተለያዩ አካባቢዎች በጦርነት የተፈናቀሉ ዜጎች መሆናቸውንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

እስከ ታህሳስ 19 ቀን 2014 ዓ.ም 128 ሺህ 584 ኩንታል እህል፣ 1 ሺህ 248 ካርቶን ብስኩት፣ ፓስታና ወተት ወደ ቀያቸው ለተመለሱት ዜጎች መድረሱንም የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

በቀጣይ በዘላቂነት በጦርነቱ የተጎዱ ወገኖችን ለማቋቋም ከተለያዩ ተቋማት፣ ዜጎች፣ በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ጋር በመሆን ለመስራት ዝግጅት መደረጉንም ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግኑኝነት ዳይሬክተሩ ተቋማት እና ግለስቦች በጦርነቱ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ ለማድረግ ሲፈልጉ በተቋሙ በኩል ብቻ መሆን እንዳለበትም አስምረውበታል።

በተለይም በአሁኑ ወቅት ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ዳያስፖራዎች እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ድጋፍ እና እገዛ ለማድረግ ሲፈልጉ በቀጥታ በኮሚሽኑ በኩል መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ከተቋሙ ውጭ የሚደረጉ ድጋፎች ፍትሀዊነት እና ታማኝነት የጎደላቸው ሊሆኑ እንደሚችሉም ነው የጠቆሙት፡፡

በሲሳይ ጌትነት

አካባቢዎን ይጠብቁ! ወደ ግንባር ይዝመቱ! መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!