አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪዉ የህዋሓት ቡድን የህልውናችን ስጋት በመሆኑ ሁልጊዜም በተጠንቀቅ ተዘጋጅተን መጠበቅ አለብን ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ መልዕክት አስተላለፉ።
ርዕሰ መስተዳደሩ በመልዕክታቸዉ ÷ ህልውናችንን ለማስከበር መላ ህዝባችን ያለምንም ልዩነት በአንድነት የከፈለው መስዋትነት የጠላትን ወረራ መቀልበስ እንዳስቻለ ሁሉ በቀጣይም ለህልውናችን ስጋት የሆነውን ወራሪ ሀይል ለመዋጋት ብቻ ሳይሆን ለውስጣችን ሰላምና ልማትም ወሳኝ በመሆኑ አንድነታችንን አጠናክረን ማስቀጠል ይገባናል ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል የከተሞቻችን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መጀመሪያ በኮረና ወረርሽኝ ፥ በመቀጠል በጦርነቱ ምክንያት በከፍተኛ ሁኔታ እየተዳከሙ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህን ችግር ለመግታት የተገኙ አማራጮችን ሁሉ በመጠቀም ኢኮኖሚውን ማነቃቃት አማራጭ ሳይሆን ግዴታ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ፥ ከዚህ አንጻር በመጭው ጊዚያት በተለይ የቱሪስት ከተማዎች የበለጠ እንዲነቃቁ ህዝባዊ በዓላትን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የዕድገት ተስፋን መፈንጠቅ አለብን ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ከመደበኛው የበዓሉ አከባበር በተጨማሪ ዲያስፖራው ከሀገር ፍቅር ስሜት በመነጨ እያደረገ ላለው ጉብኝትና ድጋፍ ለበዓሉም ሆነ ለአገራችን የተለየ ቀለምና ድምቀት እንዳለው ማስተጋባት ለውስጥም ለውጭም ዘርፈ ብዙ መልዕክት እንዳለውም መረዳት ይገባል ገልጸዋል።
ከዚህም በላይ በዓላትን በደመቀ ሁኔታ ማክበሩ በህዝባችን ላይ የደረሰውን የሥነ ልቡና ጉዳት ለመጠገን የራሱ አስተዋጽኦ አለው ነው ያሉት።
እነዚህ ሁነቶች በጦርነት የተጎዳው ህዝባችን ወደነበረበት መደበኛ ህይወት ለመመለስ ብሩህ ተስፋ የሚሰጥ በመሆኑ ጉዳዩ በመንግስት ትኩረት መሰጠቱ ተገቢ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል ብለዋል።
በአንድ በኩል ህልውናችንን ለማስከበር ፥ በሌላ በኩል የውስጥ ሰላማችንና ልማታችንን ለማፋጠን ሁላችንም እኩል ትኩረት ሰጥተን መንቀሳቀስ ቀጣዩ የትግላችን አቅጣጫ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ፥ ትግል በአንድ ወቅት የሚጠናቀቅ ሳይሆን በየምዕራፋ በቅብብሎሽ የሚቀጥል ጅረት መሆኑን አስረድተዋል።
መጭውን ጊዜ በተስፋ የሚጠበቅ የድል ፤ የሠላምና የልማት ጊዜ ለማድረግ ሁላችንም በአንድነት እንረባረብ ሲሉም መልዕክታቸዉን ማስተላለፋቸዉን አሚኮ ዘግቧል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!