የሀገር ውስጥ ዜና

የሀላባ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ በዓል ተከበረ

By Melaku Gedif

January 09, 2022

አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሀላባ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ በዓል ተከበረ፡፡

በዓሉ ለብሔረሰቡ ከዘመን መለወጫነትም አልፎ ማህበራዊ፣ ፖሊቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር በመፍጠር የብሄሩን ማንነት ለሌላው ህዝብ በማስተዋወቅ ያለው ጠቀሜታ የጎላ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በዓሉ ወጣቶች አና ልጃገረዶች የሀላባ ብሔረሰብ መገለጫ የሆኑ አልባሳትን በመልበስ ባህላዊ ሙዚቃዎችን በማዜም እና ሌሎች ትርኢቶችን በማሳየት ነው እየተከበረ የሚገኘው፡፡

በዚህ በዓል ብዙ ባህላዊ ሙዚቃዎች የሚዘወተሩ ሲሆን÷በአረንጓዴ መልክ ያሸበረቀ ቀሚስ የለበሱ እንስቶችና በተመሳሳይ መልክ ያጌጠ ቁምጣና እጀ ጉርድ ቲሸርት የለበሱ ወንዶችና ወጣት ልጃገረዶች እጃቸውን ተጠላልፈው በመያያዝ ” ሀላቢ ጮ ጩሌ” የሀላባ ቆንጆ እያሉ ያዜማሉ፡፡

የዘንድሮ የላባ ህዝብ የዘመን መለወጫ በዓል በሲምፖዚየም እንዲከበር በተወሰነው መሰረት የሀላባን ባህላዊ ምግቦችና አልባሳት በበዓሉ ላይ ቀርበው ተጎብኝተዋል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር መሀመድ ኑርዬ፥ የሀላባ ዘመን መለወጫ በዓልን በዩኔስኮ እንዲመዘገብ ጥረት እየተደረገ ባለበት ጊዜ መከበሩ የዘንድሮ በዓል ለየት ያደርገዋል ብለዋል፡፡

ይህ የሀላባ ማንነት የሚገለጥበት ልዩ የዘመን መለወጫ በዓል ባህልና ትውፊቱን ሳይለቅ እንዲከበር ሀሉም የሀላባ ተወላጅ የድርሻውን እዲወጣ ጠይቀዋል፡፡

የሀላባ የሀገር ሽማግሌዎችም የበዓሉን ባህልና ቱፊት ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ትውልዱን በማስተማር የበኩላቸውን እንደሚወጡና ባህሉ ሳይበረዝ ለዘመናት እንዲቆይ ወጣቱ ትውልድ የአባቶቹን ማንነት ተንከባክቦና ጠብቆ ማቆየት እንደሚገባው ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም ዘመኑ ያመጣቸውን ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም ለሌላው ዓለም ማስተዋወቅ አለባቸው ብለዋል።

በዓሉ በየወረዳው በየአመቱ የሚከበር ሲሆን÷በዞን ደረጃ ደግሞ በየሁለት ዓመቱ በተለያዩ ስነ-ስርዓቶች ይከበራል።

በጥላሁን ይልማ

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!