የሀገር ውስጥ ዜና

በኢትዮጵያ ከእርግዝና እና ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚሞቱ እናቶች ቁጥር እየቀነሰ ነው – ጤና ሚኒስቴር

By Alemayehu Geremew

January 09, 2022

አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ከእርግዝና እና ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ የእናቶች ሞት መጠንን በመቀነስ ረገድ ለውጦች እየተገኙ መሆኑን የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ አስታውቀዋል።

እነዚህን ለውጦች ለማጠናከርም ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

የጤናማ እናትነት ወር ከጥር 1 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የዘመቻ ንቅናቄዎች ይከበራል።

ሚኒስትሯ ዘመቻውን ምክንያት በማድረግ በሰጡት መግለጫ ÷ “ከወሊድ በኋላ በደም መፍሰስ ምክንያት የሚከሰተውን የእናቶች ሞት እጅ ለእጅ ተያይዘን እንግታ” በሚል መሪ ቃል ዘመቻው እንደሚካሄድ ተናግረዋል።

ሚኒስትሯ ÷ በኢትዮጵያ በወሊድ ምክንያት የእናቶች ሞት መጠንን ለመቀነስ በተሠሩ ሥራዎች ውጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።

በቀጣይም የተገኙ ውጤቶችን ለማጠናከር የተለያዩ ሥራዎች ይሠራሉ ብለዋል።

በኢትዮጵያ ለ16ኛ ጊዜ በሚከበረው የጤናማ እናትነት ወር በተለይም በጦርነቱ ምክንያት የተጎዱ የጤና ተቋማትን የማቋቋም ሥራዎች እንደሠሩ ሚኒስትሯ ማብራራታቸውን ኢቢሲ ዘግቧል፡፡