የሀገር ውስጥ ዜና

የደላንታ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል መልሶ ግንባታና የማደራጀት ስራ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ሊሰራ ነው

By Meseret Awoke

January 12, 2022

አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የጅማ ዩኒቨርሲቲ ጤና ኢንስቲትዩት በደቡብ ወሎ ዞን በአሸባሪው ህወሓት ጉዳት የደረሰበትን የደላንታ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የጥገና ሥራ ለማስጀመር አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን ገልጿል፡፡

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ኤልያስ ዓሊ እንደገለጹት ፥ የሽብር ቡድኑ በአማራ ክልል ጉዳት የደረሰባቸው የጤና ተቋማት በመስክ የሚገመግሙ ባለሙያዎችን ልኮ የጉዳቱን መጠን ማወቅ ተችሏል፡፡

በተደረገው የዳሰሳ ጥናትም ጉዳት የደረሰበትን የደላንታ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታልን ከአንድ ሳምንት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ጠግኖ ሥራ ለማስጀመር “የድርሻችን ለመወጣት የሚያስችል ዝግጅት አጠናቀናል” ብለዋል፡፡

እንደ ዶክተር ኤሊያስ ገለጻ የመድኃኒት፣ የህክምና መገልገያ መሰሪያዎችና የቁሳቁሶች ዝግጅት የተጠናቀቀ ሲሆን ፥ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሰጡ 30 የጤና ባለሙያዎችም ለዚሁ ስራ ተመዝግበዋል፡፡

በክልሉ ተገኝተው በጤና ተቋማት ላይ የደረሰውን ጉዳት የተመለከቱት የጅማ ዩኒቨርሲቲ ህክምና ማዕከል የቀዶ ህክምና ልዩ ሀኪም ዶክተር ታደሰ ግርማ እንዳሉት ÷በተሰራው ግምታዊ ስሌት የሽብር ቡድኑ በሆስፒታሉ ላይ ያደረሰው ጉዳት ከ75 ሚሊየን ብር በላይ እንደሚገመት ተናግረዋል፡፡

ሆስፒታሉን በማደራጀት መልሶ በፍጥነት ለህብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት እንዲችል የማድረጉ ስራ የሁሉንም የጋራ ርብርብ እንደሚጠይቅ አመልክተዋል፡፡

የጅማ ዩኒቨርሲቲ የጤና ኢንስቲትዩት በተለይም የድንገተኛ ህክምና ክፍል፣ የወሊድ እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታ ህክምና ክፍሉን ቅድሚያ በመስጠት አገልግሎት መስጠት እንዲችል ዩኒቨርሲቲው ያላሰለሰ ጥረት እያረገ መሆኑን ማስታወቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!