አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) “የቁርጥ ቀን የከተሞች እህትማማቾች ጥምረት”በሚል መሪ ቃል በጥፋት ቡድኑ ውድመት የደረሰባቸውን ከተሞች መልሶ ለማቋቋም ከተሞች አጋርነታቸውን የሚያሳዩበት መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡
በመድረኩ እህት ከተሞች በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ከተሞች ማገዝ እና ከጎናችሁ ነን ማለት እንደሚገባ ተገልጿል፡፡
በመርሃ ግብሩ የተገኙት የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ እንዳሉት፥ የሽብር ቡድኑ በከተሞች ላይ ንፁሃንን ከመግደሉ ባሻገርም የቻለውን ዘርፎ ያልቻለውን አውድሞ በመሄዱ ዜጎች ለከፋ ችግር ተዳርገዋል ፡፡
“አሸባሪውን የህወሓት ወራሪ ሃይል ኢትዮጵያውያን በአንድነት እንዳሸነፍነው ሁሉ በከተሞቻችን ላይ የደረሱ ውድመቶችን በጋራና በሃላፊነት ስሜት መልሰን ልናቋቁማቸው ይገባል” ሲሉም ገልፀዋል ሚኒስትሯ፡፡
መንግስት በሽብር ቡድኑ የደረሱ ጥፋቶችን በግብረ ሀይል ደረጃ እያጠና መሆኑን የገለፁ ሲሆን ፥ በቅርቡም ውጤቱ ለህብረተሰቡ ይፉ ይደረጋል ብለዋል፡፡
የከተሞች ተወካዮችም እህትማማችነት የትብብር ፌደራሊዝም ማሳያችን ነው፤ ዛሬም የገጠሙንን ችግሮች በጋራ እንሻገረዋለን ብለዋል፡፡
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር፣ የከተሞች ገቢ ሪፎርም ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት፣ ከኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ ጋር በመተባበር መርሃ ግብሩን አዘጋጅተዋል፡፡
በዚሁ መድረክ ከተሞች በፕላን እና መሬት ምዝገባ መረጃ ስራዎች ዙሪያ የልምድ ልውውጥ ያደርጋሉ ተብሏል፡፡
በጎህ ንጉሱ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!