የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለጭነት ቅድሚያ ቦታ ማስያዝ የሚያስችል አሰራር ጀመረ

By Meseret Awoke

January 12, 2022

አዲስ አበባ፣ ጥር4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ የካርጎ እና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ደንበኞች ለሚያስጭኑት ዕቃ በቅድሚያ ቦታ ማስያዝ የሚያስችል አዲስ አሰራር ጀመረ።

አሰራሩ ደንበኞች የበረራ መርሃ ግብሮችን ለማረጋገጥ፣ የቦታ መኖርን፣ የመጫን አቅምን እንዲሁም በነጠላ እና በሚመች መንገድ ጭነትን ወዲያው ቦታ ማስያዝ የሚያስችል መሆኑን ተገልጿል።

በዚህ መሰረትም ደንበኞች cargobooking.ethiopianairlines.com በሚለው መተግበሪያ በመግባት የተገለጹትን አገልግሎቶች ማረጋገጥ እንደሚችሉ ተመላክቷል።

የአየር መንገዱ ካርጎ እና ሎጅስቲክስ አገልግሎት የደንበኞቹን አጠቃቀም ለማሳደግ የሚያስችል የሞባይል መተግበሪያ በመጀመር ደንበኞች ቅድሚያ ቦታ እንዲይዙ እያደረገ መሆኑ የሚታወቅ ነው።

በአንድሮይድ እና በአይ.ኦ.ኤስ የሚገኘው ይኸው የሞባይል መተግበሪያ ለደንበኞች አመቺ ከመሆኑም ባለፈ ደንበኞች ራሳቸው ጊዜውን የጠበቀ ማሻሻያ ሊያደርጉበት የሚችል እንደሆነ ተገልጿል።

ይህም ደንበኞች የበረራ መርሃ ግብርን ማረጋገጥ፣ ጥያቄ ማቅረብ፣ ጭነቱ ዝግጁ ሲሆን ማሳወቂያዎችን መቀበል፣ የቻርተር በረራዎችን መያዝ እና ጭነቶችን መከታተል ያስቻላቸዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አሥፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ፥ “ለጭነት ቦታ ማስመዝገቢያ አጠቃቀም ለደንበኞቻችን ስናቀርብ ደስታ ይሰማናል” ብለዋል።

የሎጂስቲክስ እሴት ሰንሰለትን ዲጂታል በማድረግ መላው የአየር ጭነት ሂደትን ከወረቀት አሰራር ለማላቀቅ አየር መንገዱ ቁርጠኛ መሆኑን መናገራቸውንም ኢዜአ ዘግቧል።

ሂደቱን ከወረቀት አሰራር ማላቀቅ ለደንበኞች ምቹ እና ከግድፈት የፀዳ አገልግሎት የሚያስገኝ ብቻ ሳይሆን ይበልጥ ቀልጣፋ አሰራር የሚፈጥርና የአየር መንገዱን ዘላቂ ግቦችን ለማሳካት የሚረዳ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!