የሀገር ውስጥ ዜና

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ከ110 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጣ የዓይነት ድጋፍ አደረገ

By Alemayehu Geremew

January 14, 2022

አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የባሕርዳር ከተማ አስተዳደር ÷ ከከተማው ነዋሪዎች፣ ከንግዱ ማኅበረሰብ፣ ከባለሐብቶች እና ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ያሰባሰበውን ከ110ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው ምግብና የተለያዩ አልባሳት በጦርነቱ ለተፈናቀሉ እና ሐብት እና ንብረታቸው ለወደመባቸው የምስራቅ አማራ ወገኖቻችን ድጋፍ አደረገ።

የባሕርዳር ከተማ አስተዳደር የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ሃላፊ በትግሉ ተሥፋሁን ÷ ጦርነቱ በሀገራችን በተለይም በምስራቅ አማራ ያደረሰውን የንብረት ውድመትና የዜጎች መፈናቀል መልሶ ለማቋቋም እና ለመካስ በቀዳሚነት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

በዛሬው ዕለትም ለተፈናቀሉ ወገኖቻችን የሚሆን ውሃ፣በሶ፣ቴምር፣የተለያዩ አልባሳትና ሌሎችን ድጋፎች አምጥተናል ብለዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ÷ ከአሁን ቀደም ጦርነቱ በነበረባቸው ቀጠናዎች ሁሉ ቀድሞ በመድረስ ለሠራዊቱና ለተፈናቀሉ ወገኖቻችን ድጋፍ ለማድረግ ጥረት ተደርጓል በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

የሰሜን ወሎ ምክትል አስተዳዳሪና የትምህርት መምሪያ ሃላፊ ጋሻው አስማሜ በበኩላቸው ÷ የባሕርዳር ከተማ አስተዳደርና ህዝብ ፣ጠላት ዞኖቹን ከወረረ ጊዜ አንስቶ የተለያዩ ድጋፎችን በመላክ ተለይቶን አያውቅም ነው ያሉት፡፡

ዛሬም ከድል በኋላ በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውንና የተፈናቀሉ ወገኖቻችን ለመደገፍ በአካል ወልዲያ ከተማ ድረስ በመገኘታችሁ በዞኑ ህዝብና መንግስት ስም እናመሰግናለንም ነው ያሉት።

ሃላፊው አያይዘውም ÷በዞኑ ከደረሰው ሁለንተናዊ ጉዳት አንጻር ሁሉም አካል ለተማሪዎች ደብተርና እስክብሪቶ፣ለጤና ተቋማት የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጥሪማቅረባቸውን የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ በመረጃው አመልክቷል።