አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የዘንድሮ የበጋ ወራት የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ በደቡብ ጎንደር ዞን ሊቦ ከምከም ወረዳ ተጀመረ፡፡
በዘንድሮው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ልማት ስራ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ2ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ሄክታር መሬት እንደሚለማ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር እያሱ ኤልያስ ተናግረዋል።
ፕሮፌሰሩ እያሱ ይህን ያሉት የዘንድሮው ክልል-አቀፍ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃ ስራ ደቡብ ጎንደር ዞን ሊቦ ከምከም ወረዳ ሻሞ ቀበሌ ላይ በተጀመረበት ወቅት ነው።
ህዝቡን በነቂስ በማሳተፍ በርካታ የተፋሰስ ልማት ስራዎች በንቅናቄው እየተሰራ ነው ያሉት ፕሮፈሰር እያሱ ፥ ጥራት ያለው ስራ በማከናወን ተስፋ ቆርጠው ወደ ሌላ ሀገር በመሰደድ ችግር ውስጥ የሚወድቁ ወጣቶችን የስራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
አርሶ አደሩ በነቂስ ወጥቶ በተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራው በመሳተፍ የአፈር ዕቀባ ስራውን ማሳካት እንደሚገባ ጠቆመው ፥ የግብርና አመራሮችም ስራው በተገቢው መንገድ መምራት አለባቸው ተብሏል።
የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ጌታቸው ጀምበሬ፥ የክልሉን የ2014 የተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራውን አስጀምረዋል።
በሁሉም አውደ ውጊያዎች ህዝቡ እየተሳተፈ የክልሉን የልማት ስራ በተጠናከረ መንገድ ማከናወን ይገባል ብለዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሀይለማርያም ከፍአለ እንደተናገሩት ፥ በህልውና ዘመቻ ውስጥ የሚገኘው የአማራ ህዝብ ወራሪውን የትህነግ ቡድን በመደምሰስ ትልቅ ተጋድሎ ፈጥሟል።
ጠላት ያፈረሰውን የተፋሰስ ልማት መልሶ ለመጠገንና አዲሶችን ለመገንባት በዚህ ዓመት ይሰራል ያሉት የቢሮ ሃላፊው፥ በአዲስና በነባር ከ450 ሺ ሄክታር በላይ መሬት በተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራ ይለማል ብለዋል።
ከ4 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ ህዝብ በዘንድሮ የተቀናጀ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ስራ እንደሚሳተፍ የገለጹት ዶክተር ሀይለማርያም ፥ ከ8ሺ 400 በላይ ተፋሰሶች ይሰራሉ ነው ያሉት።
በመርሀ ግብሩ ላይ የተለያዩ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡
በምናለ አየነው
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!