የሀገር ውስጥ ዜና

ሁለተኛው ብሩህ የንግድ የፈጠራ ሃሳብ ውድድር ሽልማት ተካሄደ

By Meseret Awoke

January 14, 2022

አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር በተደረገ አገር አቀፍ ጥሪ ሲደረግ የነበረው ውድድር እና ስልጠና ተጠናቆ ከተመዘገቡት 462 ሃሳቦች 30ዎቹ ለሽልማት በቅተዋል፡፡

ሽልማት ያበረከቱት የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል÷ “የተመለከትናቸውን የፈጠራ ሃሳብና ውጤቶችን አግዞ ወደተግባር መቀየር ከተቻለ እንደ አገር ብሩህ የሆነ ጊዜ እንደሚጠብቀን ያሳያል” ብለዋል፡፡

ወጣቶቹ ቁጥራቸው ትንሽ ቢመስልም ኢትዮጵያ ያልተነኩ እምቅ አቅሞች እንዳሏት ማሳያ ናቸው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በወጣቶቹ የተፈጠሩት የሥራ ሃሳቦች የሥራ ዕድል ለራሳቸውም ለሌሎችም ለመፍጠር ትልቅ ጉልበት ያላቸው መሆኑን መስክረው፥ ወጣቶቹም የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች ተቋቁመው ለሌሎችም ተስፋ እንዲሆኑ አሳስበዋል፡፡

የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ንጉሡ ጥላሁን በበኩላቸው፥ ለሽልማት የበቁት የ30 የንግድ ፈጠራ ሃሳቦች ባለቤት የሆኑ ወጣቶች ሃሳባቸው ለዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥር፣ ወደ ተግባር የሚቀየር እና ችግር የሚፈታ መሆኑ ከተመረጡበት መስፈርት መካከል ይጠቀሳል ብለዋል፡፡

ወጣቶቹ የንግድ ሥርዓትን እና ክህሎትን የተመለከቱ ስልጠናዎች ተሰጥቷቸው ለሽልማት እንደበቁም ነው ያብራሩት።

ውድድሩ ከተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም እና ማስተርካርድ ፋውንዴሽን ጋር በትብብር የሚካሄድ ሲሆን፥ ተሸላሚዎች ለንግድ ፈጠራ ሃሳባቸው 5 ሺህ ዶላር ሽልማት የተበረከተላቸው መሆኑን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በብሩህ የንግድ የፈጠራ ሃሳብ ውድድር ሽልማት በመጀመሪያው ዙር 17 የንግድ ፈጠራ ሃሳቦች ለሽልማት መብቃታቸው የሚታወስ ነው፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!