አዲስ አበባ፣ ጥር 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጅማ ከተማ በማህበር ተደራጅተው መኖሪያ ቤት ለመገንባት 7 ሚሊየን ዶላር የቆጠቡ የዳያስፖራ አባላት የግንባታ ቦታ ተረከቡ።
የግንባታ ቦታው የተሰጠው በጅማ ከተማ ለመኖሪያ ቤት ልማት ከስድስት ዓመታት በፊት በማህበር ተደራጅተው ለቆጠቡ 120 የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት መሆኑ ተገልጿል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተከትሎ ወደ ሀገር ቤት የመጡ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት በጅማ ከተማ የተለያዩ ስፍራዎችን ከጎበኙ በኋላ የመኖሪያ ቤት የሚገነቡበትን ቦታ ተረክበዋል፡፡
የጅማ ከተማ ከንቲባ አቶ ነጂብ ራያ፥ ሀገራችን ፈተና ውስጥ በገባችበት ወቅት በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሀገራቸው አምባሳደር በመሆን ማገልገላቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ዳስፖራዎች ሀገራቸውን ለመገንባት የሚያደርጉት ስራ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸው፥ በሌሎች ዘርፎችም ተሳትፏቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የዳያስፖራው ማህበረሰብ ገንዘብ በማሰባሰብ ለጅማ ከተማ ልማት የ1 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር የመማሪያ ክፍሎች መገንባታቸውንም ተናግረዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ህፃናት የሚማሩበት “ቡኡረ ቦሩ” የተሰኘ ትምህርት ቤትን በከተማዋ እያስገነቡ መሆናቸውንም ነው የጠቆሙት፡፡
የጅማ ዞን ምክትል አስተዳሪ አቶ የሱፍ ሻሮ በበኩላቸው በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ ለሚፈልጉ በጅማ የተመቻቸ ሁኔታ መኖሩን ተናግረዋል፡፡
በአውስትራሊያ የኢትዮጵያ ኦሮሞ ማህበር መስራች ፀሐፊ አቶ መሀመድ አባ ዋጂ በበኩላቸው÷ የምእራባውያን ጫና ሀገራቸው ላይ ሲደርስ ሲቃወሙና ድምጻቸውን ሲያሰሙ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
እሳቸው እንዳሉት ወደ ትውልድ ሀገራችን መጥተን ሀገራችንን የመጎብኘትና የማልማት እድሉን በማግኘታችን ደስተኞች ነን ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡