የሀገር ውስጥ ዜና

በዜጎች ላይ የደረሰውን ስብራትና የንብረት ውድመት ለመጠገን ከመቼውም ጊዜ በላይ መረባረብ ያስፈልጋል – አቶ ደመቀ መኮንን

By Melaku Gedif

January 29, 2022

አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በዜጎች ላይ የደረሰውን ስብራት እና በንብረት ላይ የደረሰውን ውድመት ለመጠገን ከመቼውም ጊዜ በላይ መረባረብ ይኖርብናል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ አቶ ደመቀ መኮንን ተናገሩ፡፡

የገቢዎች ሚኒስቴር  “አገልጋይነት መገለጫችን ነው” በሚል መሪ ቃል በስራ አፈፃፀማቸው ጥሩ ውጤት ላስመዘገቡ ሰራተኞችና አመራሮች እንዲሁም ተቋማት የእውቅናና የሽልማት መርሃ ግብር አካሂዷል፡፡

በመርሃ ግብሩ የተገኙት አቶ ደመቀ መኮንን በዜጎች ላይ የደረሰውን ስብራት እና በንብረት ላይ የደረሰውን ውድመት ለመጠገን ከመቼውም ጊዜ በላይ መረባረብ ይኖርብናል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን በግንባር ፣ በዲፕሎማሲውና በኢኮኖሚው የገጠምነውን ጦርነት በአሸናፊነት ለመወጣት አንድነታችን ይበልጥ ማጠናከር ያስፈልጋል ነው ያሉት አቶ ደመቀ ፡፡

ዛሬ ላይ በሃያልነት አለምን የሚዘውሩ ሃገሮች ለጥንካሬያቸው ምንጭ ኢኮኖሚ መሆኑን የገለጹት  አቶ ደመቀ÷  ለዚህም የገቢ አሰባሰባቸው በጠንካራ የግብር አሰባሰብ ስነ ስርዓት ላይ የተገነባ  መሆኑ  ትልቅ ሚና መጫወቱን አውስተዋል፡፡

ስለሆነም  አሁን ላይ  ሀገሪቱን የጀርባ አጥንት ሆኖ የሚያሻግር ኢኮኖሚ መፍጠር ያስፈልጋል፤ ይህንንም በጠንካራ እቅድ መምራት  ተገቢ ነው ብለዋል፡፡

በዛሬው ዕለት እውቅናና ሽልማት ያገኙ  አካላትም በያዙት ሳይረኩ ለላቀ ከፍታ እንዲተጉ አሳስበዋል።

በታሪኩ ለገሰ