የሀገር ውስጥ ዜና

በአማራ ክልል የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ሳይወስዱ የቆዩ ተማሪዎች ፈተና መውሰድ ጀመሩ

By Alemayehu Geremew

February 01, 2022

አዲስ አበባ፣ ጥር 24 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል አሸባሪው ህወሓት በፈፀመው ወረራ ምክንያት የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ሳይወስዱ የቆዩ ተማሪዎች ዛሬ ፈተና መውሰድ ጀመሩ፡፡

በዚሁ መሠረት በሰሜን ሸዋ ዞን ከ1800 በላይ ተፈታኝ ተማሪዎች ፈተና መውሰድ መጀመራቸውን የሰሜን ሸዋ ዞን ትምህርት መምሪያ ሃላፊ በድሉ ውብሸት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጸዋል።

በደሴ ከተማም ፈተናውን 2 ሺህ 788 ተማሪዎች እየወሰዱ እንደሚገኝ እና 104 የሚሆኑት የግል ተፈታኞች እንደሆኑ ነው የደሴ ከተማ ትምህርት መምሪያ ሃላፊ አቶ ፍቅር አበበ የተናገሩት።

የመቄት ወረዳም ፈተናውን በአምስት አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እየሰጠ ነው።

በኮኪት አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የፈተና ጣቢያ ሃላፊ የሆኑት አቶ ፈንታው ሣኅሉ ÷ 247 መደበኛ ተማሪዎች በፈተናው ላይ መቀመጣቸውን ተናግረዋል።

ፈተናው በሚሰጥባቸው ጣቢያዎች በጸጥታ ኃይሎች ፣ በሱፐር ቫይዘሮች እና በሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት ጥበቃ እየተደረገ መሆኑንም ሃላፊዎቹ ጠቁመዋል፡፡

በአበበ የሸዋ ልዑል እና ይከበር ዓለሙ