አዲስ አበባ፣ ጥር 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በቆላማ አካባቢዎች ንጹህ የመጠጥ ውሃ ተደራሽነትን ለማስፋት በትኩረት እየሰራ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ ከ120 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ በደቡብ ወሎ ዞን ከለላ ወረዳ ከ19 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የንጹህ መጠጥ ዉሃ ፕሮጀክት ለማስገንባት ርክክብ ፈጽሟል፡፡
ለወረዳው ህዝብ ንጹህ የመጠጥ ዉሃ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ሲሆን ፣ የዚሁ አካል የሆነዉና በከለላ ወረዳ አምሥት ቀበሌዎች የሚኖሩ ከ19 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ ርክክብ መካሄዱ ተገልጿል።
ሥራውም ከ58 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያለው የመስመር ዝርጋታን ያካትታል፡፡
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በቆላማ አካባቢዎች የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝም ተመላክቷል፡፡
ግንባታው በ20 ወራት ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቅ ቀነ ገደብ የተቀመጠለት ይህ ፕሮጀክት የአካባቢዉን ነዋሪዎች ችግር ከመቅረፍ ባለፈ የወረዳዉን የንጹህ መጠጥ ዉሃ ተደራሽነት ሽፋን በማሳደግ በኩልም ሚናዉ ከፍተኛ ነው ተብሏል፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎች ÷ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ያለመኖር የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ መቆየቱንና ላልተገባ እንግልት እንዲሁም ለጤና ቀውስ መዳረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ፕሮጀክቱም ለችግራቸው መፍትሄ ይዞ እንደሚመጣ ያላቸዉን ተስፋ ገልፀዋል፡፡
የፕሮጀክቱ ግንባታ ተቋራጭ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ÷ አብርሃም ተስፋየ በበኩላቸው፥ ግንባታውን ለመጀመር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ተጠናቀው ርክክብ ተፈጽሟል ብለዋል፡፡
ሥራ አስኪያጁ ÷ በቅርቡ ወደ ተግባር እንገባለን፤ ፕሮጀክቱም በተያዘለት የጊዜ ገደብ ተጠናቆ አገልግሎት እንዲሰጥ በትኩረት እንሰራለን ብለዋል፡፡
ግንባታው ሲጠናቀቅ ከ19 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።
ሚኒስቴሩ በቀጣይ በድርቅ የተጠቁና ቆላማ አካባቢዎችን በጥናት በመለየት በዘላቂነት የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራም ተናግረዋል።
በሠላም አሰፋ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!