አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ)በጂቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ አካል የሆነ የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር አካሄደ።
የጂቡቲ ከተማ ከንቲባ ፋጡማ አወሌ በመርሀ ግብሩ ማጠቃለያ ላይ ባደረጉት ንግግር ÷ ኢትዮጵያ ባካሄደችው በአረንጓዴ አሻራ ዘመቻው ለጂቡቲ ላበረከተችው ችግኝ አመስግነዋል፡፡
የአረንጓዴ አሻራ አካል የሆነው የችግኝ ተከላ ዘመቻው የከተማቸውን ገጽታ ከመቀየር ባሻገር በቀጠናው የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም አካባቢን ለመፍጠር የሚኖረው ሚና የጎላ እንደሆነም ነው የጠቆሙት፡፡
ከንቲባዋ የኢፌዲሪ ግብርና ሚኒስቴርን አመስግነው፣ ለወደፊቱም ሁለቱ ሀገራት የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻውን በተጠናከረ ሁኔታ እንዲቀጥሉ ከፍተኛ ፍላጎታቸው መሆኑን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ በጂቡቲ የኢፌዲሪ ኤምባሲ ምክትል የሚሲዮን መሪ አምባሳደር ሞሀመድ ሀሰን ÷ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መሪ ሀሳብ የሆነውና በመላ ሀገራችን ሲካሄድ የቆየውን የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ዘመቻ ወደጎረቤት ሀገራት በማስፋፋት ስትራቴጂክ አጋራችን በሆነችው ጂቡቲም የማስቀጠል ዓላማ ያለው መሆኑን አንስተዋል።
በዚህ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ላይ የጂቡቲ ከተማ ከንቲባ ጽ/ ቤት ባልደረቦች፣ የጂቡቲ ግብርና ሚኒስቴር ተወካዮች፣ የሚስዮኑ ዲፕሎማቶች፣ እንዲሁም በጂቡቲ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ አባላት ተገኝተዋል፡፡