አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በህወሓት የሽብር ቡድን ጉዳት ደርሶባቸው ከነበሩትና በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሥር የሚገኙት ሦስት ኩባንያዎች ምርታቸውን ወደ ውጭ ገበያ ማቅረብ ጀመሩ፡፡
በፓርኩ ከሚገኙት አራት ኩባንያዎች ሦስቱ ስራ መጀመራቸው የተገለጸ ሲሆን÷ ምርታቸውን ለውጭ ገበያ ማቅረብ መጀመራቸውም ተገልጿል።
አዲዳስ እና ፑማ ለመሳሰሉ አለም አቀፍ ተቋማት ምርቶቹ የሚያቀርቡ መሆኑን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የገለጹት የኩባንያው ስራ አስኪያጅ ዎልተር ፎድሊ÷ ከ5 ሚሊየን ዶላር በላይ ውድመት ቢደርስብንም በቶሎ ወደ ስራ ገብተናል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ስራ አስኪያጁ አቶ ሙሉጌታ መኮንን በበኩላቸው የቀረው አንድ ኩባንያ በቅርቡ ስራ እንደሚጀምር ገልጸው ÷ 24 ሰዓት በማምረት ለውጭ ገበያ ምርቶች እየቀረቡ መሆኑንም ተናረዋል።
በፓርኩ ውስጥ ከሦስት ሺህ በላይ ዜጎች የስራ እድል እንደተፈጠረላቸው የተገለጸ ሲሆን÷ በሦስቱ ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ ከ90 በመቶ በላይ ሰራተኞች ወደ ስራ መመለሳቸውም ተመላክቷል።
በጣሊያን፣ በአሜሪካ፣ በቻይና ፣ በደቡብ ኮሪያና በኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች የተያዙት ኩባንያዎቹ÷ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት በኩል ሰፊ ስራ ሲሰሩ መቆየታቸውም ተገልጿል፡፡
ከሐምሌ እሰከ መስከረም ባሉት ሦስት ወራት ከ3 ነጥብ 9 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገቢ አስገኝተዋል ነው የተባለው፡፡
ካርቪኮ ኢትዮጵያ ተሰኘው ኩባንያ 69 በመቶ የሚሆነውን ገቢ የሸፈነ መሆኑም ተገልጿል።
በከድር መሀመድ