አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኅብረቱ ጉባዔ ላይ መሪዎች የአፍሪካን አንድነት የሚያጠናክሩና በአህጉሪቱ ላይ የሚታዩ የተዛቡ ትርክቶችን ለመቀየር የሚያስችሉ ሃሳቦችን ማንሳታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናገሩ።
በኅብረቱ ጉባኤ ላይ በመሪዎች የተነሱ አንኳር ጉዳዮችን በሚመለከት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።
በጉባዔው መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፤ የአፍሪካ ድምጽ በዓለም መደመጥ አለበት ሲሉ አፅኖት መስጠታቸውን ገልጸዋል።
አፍሪካ በረሃብና ጦርነት፣ በድርቅና ወረርሽኝ እየተፈተነች መሆኑን በማንሳት ለችግሮቻችን ሁሉ እራሳችን እልባት መስጠት አለብን በማለት የአፍሪካን የትብብርና አንድነት አስፈላጊነት አስምረውበታል።
አፍሪካ በጸጥታው ምከር ቤት ቋሚ መቀመጫ ሊኖራት ይገባል ሲሉም በንግግራቸው ማንሳታቸውን አምባሳደር ዲና ገልጸዋል።
ሌሎች ንግግር ያደረጉ መሪዎችም የአፍሪካን ሠላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ እውን ለማድርግ የአፍሪካዊያን ትብብርና አብሮነት በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል።
አፍሪካ ያላትን ትልቅ አቅም በትብብር ወደ ተግባር መቀየር አስፈላጊ መሆኑንም ገልጸዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
በሀገራት መካከል ትብብርን ማጠናከር፣ ግጭቶችን ማስቆም እንዲሁም በምግብ ራስን መቻል ከትኩረት ነጥቦቻቸው መካከል መሆኑን አምባሳደር ዲና ገልጸዋል።
በፓን አፍሪካኒዝም የትብብር መንፈስ ለአፍሪካ ልማት መትጋት አንድነትን ማጠናከር፤ እድገትን ማፋጠን እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።
የአፍሪካን ብልጽግና እውን ለማድርግ ከምንም አስቀድሞ አስተማማኝ ሰላምና የተረጋጋ የፖለቲካ አካሄድ ያስፈልጋል፤ ኢ-ሕገ መንግስታዊ የመንግስት ለውጥን በጋራ ማውገዝና መታገል አስፈላጊ መሆኑ ተነስቷል።
በኢትዮጵያ የተመሰረተው የአፍሪካ የበሽታዎች የመቆጣጠሪያ ማዕከል በአጭር ጊዜ ወደ ሥራ እንዲገባና የአፍሪካን ጤና ለጠበቅ ሰፊ ጥረት መደረግ እንዳለበት አብራርተዋል።
የኅብረቱ ጉባኤ መክፈቻ እነዚህና ሌሎች በርካታ ሃሳቦች የተነሱበት መሆኑን ያስታወሱት አምባሳደር ዲና÷ የመሪዎቹ ንግግር የአፍሪካን ሰላም፣ ትብብርና አንድነት የሚያጠናክር ነው ብለዋል።