አዲስ አበባ፣ የካቲት 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናዊ ትሥሥር ፕሮጀክት ከ300 ሚሊየን ዶላር በላይ በሆነ በጀት የልህቀት ማዕከላትን በመገንባት ላይ እንደሚገኝ አስታወቀ።
የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናዊ ትሥሥር ፕሮጀክት የሁለት ዓመት ተኩል አፈጻጸም ግምገማ መድረክ በሞምባሳ ኬኒያ ተካሂዷል።
ፕሮጀክቱ ከዓለም ባንክ በተገኘ ከ300 ሚሊየን ዶላር በላይ በጀት በኢትዮጵያ፣ ኬኒያ እና ታንዛንያ ውስጥ በሚገኙ 16 የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ውስጥ የልህቀት ማዕከላትን በመገንባት ላይ እንደሚገኝ ነው ያስታወቀው።
በመድረኩ በሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል የተመራ የልዑካን ቡድን ፣ የዓለም ባንክ፣ የኢንተር ዩኒቨርሲቲ ካውንስል፣ የ16ቱ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የሥራ ሃላፊዎች እና የኢንዱስትሪዎች ተወካዮች ተሳትፈዋል።
የ16 ቴክኒክና ሙያ ተቋማትና የ3ቱ ሀገራት የሁለት ዓመት ተኩል አፈጻጸም፣ የኮሌጆች ኢንዱስትሪ ትስስር ያለበት ደርጃ እና በሀገራቱ መካከል ስለሚደረገው የአሠልጣኞች ልውውጥ ላይ ውይይት ተደርጓልም ነው የተባለው፡፡
በፕሮጀክቱ የትግበራ ጊዜ ያጋጠሙ ችግሮች ተለይተው የመፍትሄ ሃሳቦች ተቀምጠዋል።
በመርሃ ግብሩ ማጠቃለያም የቴክኒክና ሙያ ተቋማትንና የኢንዱስትሪዎችን ትስስር ማሳያ የሚሆን በኬኒያ ናሽናል ኮስት ፖሊቴክኒክ ኮሌጅና በሞምባሳ ወደብ ጉብኝት መካሄዱ ከስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!