አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል ባለፋት 6 ወራት የተመዘገበው የወባ በሽታ ታማሚዎች ቁጥር በ23 በመቶ መጨመሩን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡
ቢሮው በዛሬው ዕለት የ6 ወራት የጤና ፕሮግራሞች ዘርፍ ዕቅድ አፈጻጸምን በወላይታ ሶዶ ከተማ እየገመገመ ነው፡፡
የቢሮው ምክትልና የጤና ፕሮግራሞች ዘርፍ ሃላፊ አቶ መና መኩሪያ ÷ በዘርፋ የመጡ ለውጦችን የበለጠ ማሳደግና ዝቅተኛ አፈጻጸም በታዩባቸው አካባቢዎች ማነቆዎችን ለመፍታትና ለውጥ ለማምጣት መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡
ከእናቶች የወሊድ አገልግሎት ጋር በተያያዘ በጤና ተቋማት የወሊድ አገልግሎት 80 በመቶ ማድረስ መቻሉንና የወለዱ እናቶች ሙሉ በሙሉ የድህረ ወሊድ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
ይሁን እንጂ ከወሊድ በኋላ በ24 ሰዓት ውስጥ አገልግሎት የሚያገኙ እናቶች ምጣኔ ከ58 በመቶ ያልበለጠ በመሆኑ በእናቶች ላይ የሚደርሰው የሞት አደጋ መጠን ሊጨምር ስለሚችል አገልግሎቱን ማሳደግ ይገባል ብለዋል፡፡
የሕፃናት ክትባት አገልግሎትን ያለማቋረጥ በትክክል መስጠት ቢቻል ሕፃናት ለኩፍኝ በሽታ እንደማይዳረጉም አንስተዋል፡፡
ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ባለፋት 6 ወራት በክልሉ የተመዘገበው የወባ በሽታ ታማሚዎች ቁጥር በ23 በመቶ ብልጫ አሳይቷል ያሉት ሃላፊው÷ ለዚህም የአየር ንብረት ለውጥ፣ ዝቅተኛ የአጎበር አጠቃቀምና መሰል ችግሮችን በምክንያትነት ጠቅሰዋል፡፡
ከእናቶች ክትትል ጋር በተያያዘ በየጊዜው ከፍተኛ ለውጥ እየታየ ቢሆንም በበለጠ መሥራት እንደሚያስፈልግና አንድም እናትና ጨቅላ ሕጻን በወሊድ ምክንያት እንዳታጣ ማድረግ እንደሚባ ሃላፊው ተናግረዋል፡፡
የማህጸን ጫፍ ልየታና የቅድመ ካንሰር ምርመራ ሥራዎች ላይም በቀጣይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ነው በሪፖርቱ የተመላከተው፡፡
በብርሃኑ በጋሻው