የሀገር ውስጥ ዜና

በጦርነትና በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ ተደረገ

By Meseret Awoke

February 09, 2022

አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጦርነትና በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ከ3 ሚሊየን ብር በላይ ብር የተለያዩ አካላት ድጋፍ አደረጉ፡፡

በሊባኖስ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በግጭት ለተጎዱ ወገኖች ያሰባሰቡትን 31 ሺህ 729 የአሜሪካን ዶላር (1ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ) ድጋፍ አደረጉ።

ኢትዮጵያውያኑ ድጋፉን በግጭት ለተጎዱ ወገኖች እርዳታ ለማሰባሰብ በብሔራዊ ደረጃ በተዘጋጀ አካውንት ውስጥ ማስገባታቸው ተገልጿል፡፡

የኢፌዴሪ ሚሲዮን በሊባኖስ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከዚህ በፊትም ለአገራዊ ፕሮጀክቶችና ወቅታዊ ጥሪዎች ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሶ ፥ በሊባኖስ ያለው በከፍተኛ የኢኮኖሚ ችግር ሳይበግራቸው ኢትዮጵያውያኑ ‘እኔም ለወገኔ’ በሚል መርህ ድጋፉን ማሰባሰባቸውን ጠቁሟል።

ድጋፉን ያደረጉት ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በቀጣይም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ መግለጻቸውን ከዳያስፖራ ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በሌላ በኩል የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ በሶማሌ ክልል ዘንድሮ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ለተጎጂዎች የሚሆን 1ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል።

በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ኡባህ አደን የተመራው ልኡክ በጅግጅጋ ለርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሃመድ ድጋፉን አስረክቧል ።

ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሃመድ በድጋፍ ርክክቡ ወቅት የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ በዚህ በችግር ወቅት ወገናዊነቱን በማሳየቱ አመስግነው ፥ የድርቁ ሁኔታ በቀጣይ ወራት የሚጠበቀው ዝናብ ካልተገኘ ድርቁ ከዚህ የከፋ ሊሆን ስለሚችል መንግስት ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር ዘርፈ ብዙ ጥረቶችን እያደረገ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

ሆኖም በአርብቶ አደሩ ላይ ተደጋጋሚ የሚከሰተውን ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ በግብርና በመስኖና በውሃ ከርሰምድር ጥናቶች ላይ ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ሙያዊ እገዛው እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል ።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ኡባህ አደን በበኩላቸው የተደረገው ድጋፍ የመጀመሪያ መሆኑን ጠቅሰው ፥ በቀጣይ በተለያዩ አስፈላጊ በሆኑ በቁስና በሙያዊ ድጋፎችን ለማድረግ ከክልሉ መንግስትና ህዝብ ጎን መሆናቸውን አስታውቀዋል ።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!