አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ከህልውና ዘመቻው ጎን ለጎን በተካሄደ የበጋ የመስኖ ልማት ስራ ከእቅድ በላይ ማሳካት መቻሉን የዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡
በመምሪያው የመስኖ ልማት የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ሃውልቱ ታደሰ ለኢዜአ እንደገለጹት ፥ በአካባቢው የሰፈነው ሰላም ለመስኖ ልማት ስራው ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡
በዚህም በመጀሪያው ዙር 20 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ 20 ሺህ 282 ሄክታር በማልማት ከዕቅድ በላይ ማሳካት መቻሉን ገልጸዋል።
የመስኖ ልማቱ ውጤታማ እንዲሆን 34 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያና ምርጥ ዘር በማሰራጨት አርሶ አደሩ ሙሉ ጊዜውን ለመስኖ ልማቱ እንዲያውል መደረጉን ተናግረዋል፡፡
በልማቱ የተሳተፉ ከ70 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች አዳዲስ የግብርና አሰራሮችንና ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀሙ መደረጉን ጠቁመዋል።
እንዲሁም ለመስኖ ስራው የሚያግዙ እያንዳንዳቸው 100 ሄክታር መሬት የማልማት አቅም ያላቸው ሦስት የውሃ መሳቢያ ሞተሮች ጥቅም ላይ መዋላቸውንም አስረድተዋል፡፡
እንደ ሩዝ፣ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ገብስ፣ ሽንኩርት፣ ድንች፣ ቲማቲምና ጥቅል ጎመን የመሳሳሉት ገበያ ተኮር ሰብልና አትክልት በስፋት መልማታቸውንም ተናግረዋል።
ከመስኖ ልማቱ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ገልጸው ፥ የመስኖ ልማቱ የአካባቢውን የግብርና ምርት አቅርቦት በማሻሻል የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡
አርሶ አደሮቹ በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት፥ በአንድ ሄክታር መሬት ሽንኩርትና ቲማቲም አልምተው ለገበያ ለማቅረብ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ ያለሙት የስንዴ ቡቃያ በጥሩ ደረጃ ላይ ስለሚገኝ 20 ኩንታል ምርት ሊያገኙ እንደሚችሉ ተናግረዋል።
ማዕከላዊ ጎንደር ዞን በከርስ ምድርና በገፀ ምድር ውሃ በበመስኖ መልማት የሚችል ከ50 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት እንዳለ ከዞኑ ግብርና መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!