አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በተባበሩት መንግስታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት በጋምቤላ ክልል ባለፈው ክረምት በጎርፍ ለተጎዱ ወገኖች ከ13 ሚሊየን ብር በላይ የጥሬ ገንዝብ ድጋፍ አደረገ።
በጋምቤላ የተራድኦ ድርጅቱ ተጠሪ ዶክተር አብዱልሀቅ ዋሂድ እንደገለጹት፥ ዩኒሴፍ ድጋፉን ያደረገው ባለፈው ክረምት በአምስት ወረዳዎች ተከስቶ በነበረው ጎርፍ ጉዳት ለደረሰባቸው 5 ሺህ 800 ወገኖች ነው።
ለቀጣይ ሦስት ወራት የምግብ ፍጆታ የሚውል 13 ሚሊየን 192 ሺህ ብር መለገሱ የተገለጸ ሲሆን፥ ድርጅቱ የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተጠሪው ተናግረዋል።
ለእያንዳንዱ ተጎጂ በየወሩ 700 ብር እንደሚሰጥ ተጠቁሟል፡፡
በክረምቱ ወራት የደረሰው የጎርፍ አደጋ ሰብላቸውንና ንብረታቸውን ያወደመባቸው ተጎጂዎችም የተሰጣቸው የገንዘብ ድጋፍ የምግብ እጥረት ችግራቸውን ሊያቃልላቸው እንደሚችል ጠቁመው፥ ድርጅቱ ላደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።