የሀገር ውስጥ ዜና

አምባሳደር ሬድዋን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን መልዕክት ለፓኪስታኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አቀረቡ

By Alemayehu Geremew

February 22, 2022

አዲስ አበባ፣ የካቲት 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ካህን የተላከን መልዕክት አቅርበዋል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን የሚመራው ልዑክ በፓኪስታን እያደረገ በሚገኘው ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ከሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ካህን ጋር ተወያይቷል።

ሚኒስትር ዴኤታው ከጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ካህን ጋር በነበራቸው ቆይታ ፓኪስታን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት ስብሰባ ወቅት ለኢትዮጵያ ለሰጠችው ድጋፍ ምስጋናቸውን ገልጸዋል።

አክለውም ሁለቱ ሀገራት በሁልትዮሽና እና በባለብዙ ወገን መድረኮች በሚያደርጓቸው ትብብሮች ለግንኙነታቸው የበለጠ መጠናከር ጽኑ መሰረት መጣላቸውን ጠቅሰዋል።

በተያያዘም ሁለቱ ሀገራት በንግድ፣ ኢንቨስትመንትና ዓለም አቀፍ ሰላም ጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያደርጉት ትብብር በየጊዜው እያደገ መምጣቱን ጠቅሰው፥ ኢትዮጵያም ይህን የግንኙነት ደረጃ ከግምት በማስገባት ኤምባሲዋን በኢስላማባድ ለመክፈት መወሰኗን ተናግረዋል።

በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የወዳጅነት ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከርም የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ካህን ኢትዮጵያን አንዲጎበኙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የላኩትን ግብዣ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ካህን በበኩላቸው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለላኩላቸው የመልካም ምኞትና የወዳጅነት መልዕክት እንዲሁም ላደረጉላቸው የጉብኝት ግብዣ ምስጋናቸውን ገልጸዋል።

ፓኪስታን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ግንኙነት ትልቅ ዋጋ የትምሰጠው መሆኑን ጠቅሰው፥ ሁለቱ ሀገራት በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፎች ያላቸውን ትብብር የበለጠ ለማጠናከር መሰራት እንዳለበትም ጠቁመዋል።