የሀገር ውስጥ ዜና

አስተዳደሩ ሀገራዊ ፋይዳ ባላቸው በሳይበርና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ከተሰማሩ ተቋማት ጋር እንደሚሠራ ገለጸ

By Meseret Awoke

February 28, 2022

አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢንፎርሚሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ግለሰቦች እንደሚደግፍ እና ሀገራዊ ፋይዳ ባላቸው በሳይበርና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ከተሰማሩ ተቋማት ጋር በጋራ እንደሚሠራ የአስተዳደሩ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛው ገለጹ፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ ይህን ያሉት በቅርቡ በግሉ ሰዉ አልባ አውሮፕላን የሰራዉ መምህር አማኑኤል ባልቻ እና የደንቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት የኢንፎርሚሽን መረብ ደህንነት አስተዳደርን በጎበኙት ወቅት ነው ተብሏል፡፡

ውጤታማ የፈጠራ ሥራ ያበረከተውን የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ መምህር አስተዳደሩ በሰዉ ኃይል እና በማቴሪያል በመደገፍ ዓላማዎቹ እንዲሳኩ እና በቴክኖሎጂው ዘርፍ ተጠቃሚ መሆን እንዲችል የድርሻውን እንደሚወጣ ዋና ዳይሬክተሩ አረጋግጠዋል።

አስተዳደሩ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተሰጥኦ ያላቸዉን ታዳጊዎች በተቋሙ ውስጥ ባለዉ የተሰጥዎ ማዕከል እያበቃ እንደሚገኝ ጠቅሰው፥ እንደ አማኑኤል ያሉ የፈጠራ ባለቤቶችም በአስተዳደሩ ውስጥ ያሉትን አቅሞች መጠቀም እንደሚችሉ ገልጸዋል።

የደንቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ለታ ተስፋዬ በበኩላቸው፥ አስተዳደሩ ይህን እድል መፍጠሩን አመስግነዉ በዩኒቨርሲቲዉ ያሉ እና ተሰጥኦ ያላቸውን ሌሎች ተማሪዎችንም በማሰባሰብ በጋራ የምንሰራበት አማራጭ እንፈጥራለን ማለታቸውን ከአስተዳደሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!