የሀገር ውስጥ ዜና

መጋቢት ወር ለሚካሄደው የብልፅግና ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤ ዝግጅቶች እያጠናቀቁ መሆኑን የተለያዩ ክልሎች የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች አስታወቁ

By Alemayehu Geremew

March 01, 2022

አዲስ አበባ፣የካቲት 22፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በቀጣይ መጋቢት ወር መጀመሪያ ለሚካሄደው የብልፅግና ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤ ዝግጅቶች እየተጠናቀቁ መሆኑን የደቡብ፣ የጋምቤላ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልሎች እንዲሁም የድረዳዋ ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ሃላፊዎች አስታውቀዋል፡፡

ለጠቅላላ ጉባኤው የዝግጅት ኮንፈረንስ እየተካሄደ የሚገኘው “ከፈተና ወደ ልዕልና” በሚል መሪ ቃል መሆኑን ክልሎቹ ገልፀዋል።

በደቡብ ክልል እስከ አሁን ከ2 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ የሚሆኑ የፓርቲው አባላት ኮንፈረንስ አካሂደው የጉባዔ ተሳታፊ ተወካዮችን መምረጣቸውን የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ጽኅፈት ቤት ሃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ ተናግረዋል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በፓርቲው አባላት ዘንድ የታዩ የአመለካከት ችግሮች የሚቀረፉበትና ጠንካራ አደረጃጀት የሚፈጠርበት ስልት መነደፉንም ሃላፊው ተናግረዋል።

በክልሉ 253 በድምጽና 25 ያለ ድምጽ የሚካፈሉ ተሳታፊዎችም መመረጣቸው ነው የተመለከተው፡፡

በሌላ በኩል የጋምቤላ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ሁሉም አባላት የሚሳተፉበትና በቅርቡ የሚካሄድ ጉባዔ አካል የሆነ የመሠረታዊ ፓርቲ ኮንፈረንስ እያካሄደ እንደሚገኝ የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ላክዴር ላክባክ ተናግረዋል፡፡

ሃላፊው÷ የኮንፈረንሱ ዓላማ በፓርቲው ውስጥ ዴሞክራሲን ለማረጋገጥ የሚያግዝና ያለፉ የለውጥ ዓመታት ጉዞ በዝርዝር የሚገመገምበት ነው ብለዋል።

የጋምቤላ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ አባልና የክልሉ ርዕሠ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ፥ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ደረጃ በሚመለከት ያጋጠሙ እና እያጋጠሙ ያሉ ፈተናዎችን መሻገር የሚያስችል ብቁ አመራርና አሠራር ለመፍጠር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት እንደሚደረግም ገልፀዋል።

በተመሳሳይ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የክልል ማዕከል የአባላት ኮንፈረንስ መካሄድ መጀመሩን አስታውቋል፡፡

በኮንፈረንሱ የብልፅግና አባላት ፓርቲው ህገ ደንብ ላይ ተወያይተው ያዳብራሉ ፣ በኮንፍረንሱ ጉባኤ የሚሳተፉ አባላትን ምርጫ ይካሄዳሉ ቀጣይ አቅጣጫዎችንም ያስቀምጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የድሬዳዋ ብልፅግና ፓርቲ በመሠረታዊ ፓርቲ ደረጃ ኮንፍረንስ እያካሄደ እንደሚገኝ መገለፁን ከክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ፅኅፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡