አዲስ አበባ፣ የካቲት 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ቤጂንግ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሚሲዮን ለ126ኛ ጊዜ የሚከበረውን የዓድዋ ድል በዓል በቻይና ከሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላትና በቻይና ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ጋር በዌብናር አክብሮ ውሏል።
በበዓሉ በቻይና የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር÷ ኢትዮጵያን ለዚህ ታላቅ ድል ያበቃት መላው ኢትዮጵያዊ ጾታ፣ ብሄርና ሃይማኖት ሳይለየው ሆ ብሎ በአንድነት ከጫፍ ጫፍ ተነስቶ በመዝመቱ ነው ብለዋል፡፡ አያይዘውም የዓድዋ ድል ለፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ እንደመስፈንጠሪያና ትልቅ ማነቃቂያ ሆኖ ያገለገለና ከኢትዮጵያውያን አልፎ በመላው አለም ለሚገኙ ጥቁር ህዝቦች በተለይም ለአፍሪካዊያን ኩራትን ያጎናፀፈ ነው ብለዋል፡፡