የሀገር ውስጥ ዜና

በአንድነት በመቆም ብልጽግናን እውን ማድረግ እንደሚቻል የዓድዋ ድል ትምህርት ይሆናል – አቶ ታገሰ ጫፎ

By Alemayehu Geremew

March 02, 2022

አዲስ አበባ፣ የካቲት 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) 126ኛው የዓድዋ ድል በዓል በጦርነት ብቻ ሳይሆን ድህነትን ለመዋጋት በአንድ ከቆምን ብልጽግናን እውን ማድረግ እንደሚቻል ትምህርት የሚሆን የድል በዓል መሆኑን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ገለጹ፡፡

አፈ-ጉባዔ ታገሠ ጫፎ በዱባይ ኤክስፖ 2020 ላይ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በ1888 በዚህ ቀን ኢትዮጵያውያን ከአራቱ ማዕዘን በመትመም በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የተሰባሰቡበትና ኢትዮጵያን ቅኝ ለመግዛት የመጣውን የጣሊያን ወራሪ ድል የመቱበት ቀን መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የተገኘው ድል ምስራቅ አፍሪካን ቅኝ ለመግዛት ያሰፈሰፈውን ቅኝ ገዢ ኃይል ያሳፈረ እንደነበረና የኢትዮጵያውያኑ ድል ለዜጎች ብቻ ሳይሆን ለጥቁር ህዝቦች በጠቅላላ ነጻነትን ያጎናጸፈ እና በመከባበር እና በአንድነት ከተነሱ ነጭን ድል ማድረግ እንደሚቻል ያሳየ ነው ብለዋል፡፡

የዓድዋ ድል በጦርነት ብቻ ሳይሆን ድህነትን ለመዋጋት በአንድ መቆም እንዳለብንና መሻሻሎችንና ብልጽግናን እውን ማድረግ እንደሚቻል ያሳየ ድል መሆኑንም አስረድተዋል።

አፈ ጉባዔው ኢትዮጵያ ከአረብ ኢሚሬቶች ጋር ያላት ታሪካዊ እና በወዳጅነት ላይ የተመሰረት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከነቢዩ መሐመድ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ጀምሮ የነበረ እና የቀጠለ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

በወቅቱ ኢትዮጵያ ነቢዩን ተከትለው ለመጡት መጠለያ ሰጥታ ሐይማኖታቸውን እንዲያካሂዱ መፍቀዷንም አፈ-ጉባዔው አንስተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ያለው ነጃሺ መስጊድ ለዚህ ቋሚ ምስክር መሆኑንም በንግግራቸው ጠቅሰዋል።

ሁለቱ ሀገራት በንግድ ፣ ኢንቨስትመንት እና በሌሎች ዘርፎች ሁሉ በትብብር የዕድገት እስትራቴጂ ነድፈው የሚሰሩ ሀገራት እንደሆኑና የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች በንግዱ ዘርፍ 1 ቢሊየን ዶላር የሚደርስ መዋዕለ-ንዋይ አፍስሳ እየሰራች እንደምትገኝም ነው የተናገሩት።

አያይዘውም በንግድ ኤክስፖው ኢትዮጵያ “ምድረ ቀደምት” በሚል ሥያሜ አውደ ርዕይ እየተካፈለች እንደምትገኝ ጠቁመው፥ ሥያሜው ኢትዮጵያ ቀደምት የሰው ልጅ መገኛ እንደሆነች ፣ የበለጸገ ባሕል ባለቤት እና በርካታ የኢንቨስትመንት ዕድሎች ያላት ሀገር እንደሆነች የሚያመላክት መሆኑን አስረድተዋል።

በዓውደ ርዕዩ የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሐብቶች እሴት ተጨምሮባቸው፣ የሀገሪቷ ኢንዱስትሪ፣ የባሕል ብዝሃነት፣ ቡና እንዲሁም ጥንታዊ የሰው ልጅ መገኛ መሆናችንን የምትመሰክረውን “ሉሲ” ድንቅነሽ እና ሌሎች የኢትዮጵያ መገለጫዎች ለዕይታ መቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ የበርካታ የቱሪዝም መዳረሻዎች ሀገር እንደሆነችና በንግዱ እና በሌሎች በርካታ ዘርፎች ላይ መዋዕለ-ንዋያቸውን ማፍሰስ ለሚፈልጉ ባለሐብቶችም ያልተነኩ አማራጮች ያላት ሀገር እንደሆነች አመላክተዋል።

የዱባይ 2020 ኤክስፖ ለዓለም ሀገራት ማኅበረሰብ ባሕል፣ እሴት ፣ ታሪክ እና የተፈጥሮ ሐብት እውቅና በመስጠት በአንድ ላይ ማገናኘት፣ ሀገራቱን ማስተዋወቅ፣ በመካከላቸውም የትብብርና የወዳጅነትን መንፈስ ለማጠናከር ብሎም ሀገራቱ ለችግሮቻቸው ዘላቂ መፍትሄ እንዲሹ እና የተሻለ ዓለም ዕውን ማድረግ እንዲቻል የተፈጠረ ምኅዳር ነው፡፡