አዲስ አበባ፣ የካቲት 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሞጆ ከተማ አስተዳደር በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን በተከሰተው ድርቅ ለተጎዱ ወገኖች 2 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር ግምት ያለው የምግብ እህል ድጋፍ አደረገ።
ድጋፉን የሞጆ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ፀጋዬ ተክለሃና ለምሥራቅ ሐረርጌ ዞን አስተዳዳሪ ሚስኪ መሐመድ አስረክበዋል።
አስተዳዳሪዋ በወቅቱ እንደተናገሩት፣ በዞኑ ከዝናብ እጥረት ጋር በተያያዘ አምሥት አርብቶ አደር ወረዳዎች ላይ ድርቅ ተከስቷል፤ በዚህም በወረዳዎቹ የሚገኙ ነዋሪዎችና እንስሳት ለችግር መጋለጣቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የከተማው አስተዳደር በችግር ውስጥ ለወደቁት ወገኖች ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የዞኑ አደጋ ስጋት አመራርና የልማት ተነሺዎች ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ኑሬ መሐመድ በበኩላቸው ÷ በድርቁ በተለይ በዜጎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ በመንግሥት፣ በዞኑ ሕዝብና ለጋሾች ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አሁን ባለው ሁኔታም ለተጎጂዎች የሚደርሰው ድጋፍ በቂ ባለመሆኑ ሁሉም የሚያደርገውን የምግብ ፣ የእንስሳት መኖና የውሃ አቅርቦት ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
የሞጆ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ÷ በዞኑ በተከሰተው ድርቅ ለተጎዱት ዜጎች የሚውል 900 ኩንታል እህል ድጋፍ ማምጣታቸውን በመርሃ-ግብሩ ላይ ተናግረዋል።
ድርቁ በዞኑ ከህዝቡ በተጨማሪ እንስሳቱም ላይ ጉዳት ማስከተሉን መገንዘባቸውን ገልጸው፤ በቀጣዩ ሳምንት የእንስሳት መኖ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጅት ላይ እንደሚገኙም አስታውቀዋል።