አዲስ አበባ፣የካቲት 25፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ወራሪው የትህነግ ቡድን ጉዳት ካደረሰባቸው በደሴ ዲስትሪክት ሥር የሚገኙ 23 የኤሌክትሪክ አገልግሎት መስጫ መዕከላት ኃይል ማግኘታቸው ተገለጿል፡፡
በወገልጤና አከባቢ የምትገኘው እና ከፍተኛ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ውድመት ከደረሰባት ፀሀይ መውጫ ሳተላይት በስተቀር ሁሉም አገልግሎት መስጫ ማእከላት እና ሳተላይት ጣቢዎች በአሁኑ ሰዓት አገልግሎቱን እያገኙ መሆናቸው ተጠቅሷል።
የአማራ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮሙዩኒኬሽን ክፍል ሰሞኑን በወራሪው ቡድን ወድመት የደረሰባቸውን የወልድያና ደሴ ዲሰትሪክቶች ያሉበትን ሁኔታ በመስክ ምልከታ ተዘዋውሮ ተመልክቷል፡፡
የደሴ ዲስትሪክት ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አበበ በዚህ ወቅት በሰጡት ማብራሪያ፥ በአሸባሪው የትህነግ ቡድን በደሴና አካባቢዎቹ ያደረሰው ጉዳት ከፍተኛ እንደነበር አስታውሰው፥ ቡድኑ በለቀቀ ማግስት ዲሰትሪክቱ የመልሶ ግንባታ ስራዎችን ለመስራት በፍጥነት በመጀመር ደንበኞች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረጉን ገልፀዋል፡፡
በዲሰትሪክቱ ቅድሚያ 21 አገልግሎት መስጫ ማዕከላቶች ብቻ ኃይል ማግኘታቸውን ያወሱት ዳይሬክተሩ ሁለቱ ማዕከላት ዉጫሌና ወገልጤና በወልድያ 66ኪቪ ሰብስቴሽን ብልሽት ምክንያት ወዲያውኑ ማግኘት አልቻሉም ነበር ብለዋል፡፡ የወልድያ ሰብሰቴሽን ወደስራ እንደገባ የውጫሌና ወገልጤና አገልግሎት መስጫ ማዕከላት አካባቢዎች አገልግሎቱን አግኝተዋል ብለዋል፡፡
አንዳንድ ሳተላይት ጣቢዎች ላይ ከጉዳቱ ስፋት አንፃር በወቅቱ አገልግሎቱን በፍጥነት መስጠት ሳይቻል ቢቀርም የወረዳ ከተሞች አገልግሎት ማግኘት ከጀመሩ በኋላ ደረጃ በደረጃ እንዲያገኙ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡
በመሆኑም በወገልጤና አከባቢ የምትገኘው እና ከፍተኛ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ውድመት ከደረሰባት ፀሀይ መውጫ ሳተላይት በስተቀር ሁሉም አገልግሎት መስጫ ማእከላት እና ሳተላይት ጣቢዎች በአሁኑ ሰዓት አገልግሎቱን እያገኙ መሆኑን ገልፀው የፀሀይ መውጫ ከተማ የምሰሶ ተከላ ስራ ተጠናቆ የመስመር ዝርጋታ ስራ እየተከናወነ መሆኑን እና በቅርቡ የምታገኝ መሆኑን ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ደንበኞች የተጠቀሙበትን ኤሌክትሪክ ፍጆታ በሞባይ ባንኪንግ፣ በሲቢኢ ብር፣ በቴሌብር ወይም ሌሎች አማራጮችን በመጠቀም እንዲከፍሉ ያሳሰቡ ሲሆን ሌሎች መደበኛ አገልግሎቶችን ለማግኘት በአቅራቢቸው ባሉ የደንበኞች አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ማግኘት እንደሚችሉ መግለፃቸውን ከአማራ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!