አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሱዳን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ ከሱዳን የፌደራል አስተዳደር ሚኒስትር ቡሲና ኢብራሂም ዲናር ጋር ዛሬ በፅህፈት ቤታቸው ተገናኝተው በኢትዮጵያ እና በሱዳን ተጐራባች ክልሎች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር በሚረዱ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
በዚህ መሠረት አምባሳደሩ በሱዳን እና በኢትዮጵያ ተጐራባች ክልሎች እና ሕዝቦች መካከል የሚደረግ ትብብር እና ግንኙነት በአጠቃላይ ለሁለቱ አገሮች ግንኙነት ትልቅ ፋይዳ ያለው በመሆኑ ተቀራርቦ መስራት አስፈላጊ እንደሆነ አንስተዋል።
በማያያዝም የሁለቱ አገራት ተጎራባች ክልሎች ሕዝቦችን እና አስተዳዳሪዎችን በበለጠ የሚያቀራርቡ የንግድ፣ የባህል እንዲሁም የድንበር ፀጥታና ሠላም ተግባራትን ተባብሮ ማከናወን ጠቃሚ እንደሆነ በመጥቀስ፥ በዚህ ረገድ ከዚህ ቀደም በተጐራባች ክልሎች መካከል ያለውን ሁለንተናዊ ትብብር ለማጠናከር የተቋቋሙ የትብብር መድረኮችን ማንቀሳቀስ እንደሚገባ ጠቅሰዋል።
ሚኒስትር ቡሲና በበኩላቸው በሁለቱ አገራት መካካል ያለውን ታሪካዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ይበልጥ ተቀራርቦ መስራት አስፈላጊ እንደሆነና ከዚህ አንጻር በቅርቡ የሱዳን የብሉናይል ግዛት አስተዳዳሪ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ያደረጉት ጉብኝትም ውጤታማ እንደነበር አንስተዋል።
ሚኒስትሯ በማያያዝም የጋራ ድንበር ንግድን ለማጠናከር የጋራ የግብይት ቦታዎችን ማመቻቸት አስፈላጊ እንደሆነ እና በታችኛው የአስተዳደር መዋቅር የሚገኙ አከላት ወቅታዊ ግንኙነቶች እንዲደረጉ ማበረታታት እንደሚገባ ነው የተናገሩት።
የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እንዲረዳም የባህል ልውውጥ መድረኮችን ማመቻቻት ጠቃሚ እንደሆነ ሚንስትሯ አክለው መግለፃቸውን ከኤምባሲው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።