የሀገር ውስጥ ዜና

በመዲናዋ በቡድን በመደራጀት እና በተናጠል ተሽከርካሪዎችን ሲሰርቁ የነበሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

By ዮሐንስ ደርበው

March 08, 2022

የመኪና ስርቆትን ለማስቆም እና ፈፃሚያቸውን ለመያዝ የልዩ ልዩ እና የተደራጁ ወንጀሎች ምርመራ ዳይሬክቶሬት ከክትትል ክፍሉ ጋር በመቀናጀት ባደረገው ጥረት በሶስት ቡድን የተደራጁ 16 ተጠርጣሪዎችን እና በተናጠል የመኪና ስርቆት ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ 5 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል ነው ያለው።

በአዲስ አበባ ፖሊስ የወንጀልና ትራፊክ አደጋ ምርመራ ዘርፍ የተደራጁ ወንጀሎች ምርመራ ዲቪዚዩን ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ያሬድ አለማየሁ፥ ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ በተከናወነው ምርመራ የማስፋት ስራ ቀደም ሲል ፈፃሚያቸው ባልታወቀ የተመዘገቡ ወንጀሎች በእነዚህ ተጠርጣሪዎች እንደተፈፀሙ በማረጋገጥ የተሰረቁትን ተሽከርካሪዎች ማስመለስ ተችሏል ብለዋል።

በዚህም በተለያየ ጊዜ የተሰረቁ ከሚኒባስ እስከ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ለባለንብረቶቹ ማስመለስ መቻሉን ጠቅሰው፥ የተወሰኑ ተሽከርካሪዎች የውስጥ እቃዎቻቸው ተሸጦ መገኘታቸውንም አስረድተዋል።

አሁን ላይም ተጠርጣሪዎቹ በ10 መዝገቦች ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ ያመላክታል።

የተሽከርካሪ ባለንብረቶችም አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ የበኩላቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ ፖሊስ ጥሪውን አቅርቧል።